ቀጥታ፡

ኅብረቱ ምርጫው በሠላም መጠናቀቁን አረጋግጫለሁ አለ

ሰኔ 16/2013 (ኢዜአ) ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሠላማዊ ሆኖ መጠናቀቁን አረጋግጫለሁ ሲል የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ሕብረት ለምርጫ ገለፀ።

ኅብረቱ የመጀመሪያ ዙር ሪፖርቱን ዛሬ ይፋ አድርጓል።

ለአገራዊ ምርጫው በሰባት ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ከሦስት ሺህ በላይ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎችን አሰልጥኖ ማሰማራቱን ገልጿል።

የኅብረቱ የቦርድ አባል አቶ ሳህለስላሴ አበበ 'ምርጫው ሠላማዊ ሆኖ ማለፋን ካሠማራናቸው ታዛቢዎች ከደረሰን ሪፖርት አረጋግጠናል' ብለዋል።

በዋናነት በድምፅ መስጠት ሒደት ከታዩ በጎ ጎኖች መካከል ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተከሰቱ ክፍተቶችን ለመሙላትና ወቅታዊ ምላሽ ለመስጠት ጥረት ማድረጉን አድንቀዋል።

መራጩ ሕዝብም በነቂስ በመውጣት መሳተፉና ድምፁን ለመስጠት በትዕግስት መጠባበቁ እንዲሁም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሒደቱ በሠላም እንዲጠናቀቅ ያደረጉትን አስተዋፅኦ በመልካም ጎን የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

በምርጫ ጣቢያዎች ሴቶች ንቁ ተሳትፎ እንደነበራቸው የገለጹት አቶ ሳህለስላሴ ኅብረቱ የምርጫ ጣቢያዎች በተቻለ መጠን ለአካል ጉዳተኞች፣ ህጻናት ለያዙ እናቶች፣ ለአረጋዊያንና ለአቅመ ደካሞች ምቹ እንዲሆኑ መደረጋቸውን ኅብረቱ መታዘቡንም ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል በጥቂት ቦታዎች የምርጫ ጣቢያዎች ዘግይተው መከፈት፣ የቁሳቁስ መጓደልና በዚህም ሳቢያ በመራጮች ላይ የደረሰውን መጉላላት ኅብረቱ መታዘቡን አቶ ሳህለስላሴ ጠቅሰዋል።

በጥቂት የምርጫ ጣቢያዎችም እንዲገኙ የማይፈቀድላቸው ሰዎች መገኘታቸውና የምርጫ ቅስቀሳ ሁኔታዎች መስተዋላቸውን ተናግረዋል።

ሕብረቱ በቀጣይ ሁለተኛ ዙር ሪፖርት ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም