ቀጥታ፡

የምርጫው በሰላም መጠናቀቅ የኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ እንደማይደራደሩ ያሳየ ነው--ምሁራን

ደሴ፤ ሆስዕና ፤ሰኔ 16/2013 (ኢዜአ) ምርጫው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ መጠናቀቁ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጉዳይ እንደማይደራደሩ በተግባር ያሳየ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

በሌላ በኩል  ምርጫው በማሸነፍ አዲስ የሚመሰረተው መንግስት የሀገሪቱን ዜጎች በእኩልነት ለማገልገል  ትኩረት እንዲሰጥ  በሀድያ ዞን ነዋሪዎች ጠየቁ።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር አቶ ጀማል ሰይድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላምና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግስትና ምርጫ ቦርድ ያደረጉት ቅደመ ዝግጅት የሚደነቅ ነበር፡፡

ተፎካካሪ ፓርቲዎችም  ያገኙትን ነጻነት ተጠቅመው ፕሮግራምና ዓላማቸውን ብቻ ለህዝብ ለማስተዋወቅ ያደረጉት ጥረትና ትብብር የዲሞክራሲ ምህዳሩን ያሰፋ ነው ብለዋል፡፡

ምርጫ ቦርድም ገለልተኛ ሆኖ ለሚስተዋሉ ክፍተቶች የሚወስደው ፈጣን የማስተካከያ እርምጃ የተቋሙን አቅምና የዴሞክራሲ ፍላጎት አጉልቶ በማሳየቱ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ሁሉም የየድርሻውን ተወጥቶ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ማድረጉም ኢትዮጵያዊያን በጥቃቅን ጉዳዮች ሳይለያዩ በሀገራቸው ጉዳይ እንደማይደራደሩ በተግባር እንዳሳዩ ገልጸዋል።

የውስጥና ውጭ ጠላቶችም በምርጫው ሰበብ ህብረተሰቡን  በብሔርና በእምነት ከፋፍለው ሀገር ለማፍረስ ቢታክቱም በህብረተሰቡ ሰላም  ወዳድነት መክሸፍን አመልክተዋል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሀገርና ህዝብን አስቀድመው በሰላም እንዲጠናቀቅ ማድረጋቸውን እንደሚያደንቁ የገለጹት ምሁሩ፤ በህዝብ ድምጽ የሚያሸንፈው ፓርቲ ለቀጣይ የህዝብ ጥያቄዎች መዘጋጀት ይኖርበታል ብለዋል።

እርሳቸውም ያለ ማንም አስገዳጅ ለሚፈልጉት ፓርቲ ድምጻቸውን በነጻነት መስጠታቸውን ጠቅሰው፤ ምርጫው ሰላማዊ፤ ተዓማኒና ነጻ ለመሆኑ ምስክር ነን ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሰላም፤ ዲሞክራሲና ልማት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አልዩ ውዱ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በሴራ ፖለቲከኞች ሳይታለል ሰላምና አንድነቱን ጠብቆ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ አድርጓል ብለዋል።

በዚህም ለሀገሩ ያለውን ፍቅርና ለጠላት የማይንበረከክ መሆኑን በግልፅ ማሳየት ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

ለምርጫው የተሰጠው ነጻነትና የመንግስት ቁርጠኝነት በተለየ መልኩ ተዓማኒ፤ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ማስቻሉን ጠቁመው ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ያሳዩት ትብብርና ቁርጠኝነት ጠላቶችን አሳፍሯል ብለዋል።

ተፎካካሪ ፕርቲዎችም ምንም ይሁን ምን ውጤቱን በፀጋ ተቀብለውና አሸናፊውን ፓርቲ ደግፈው ሀገሪቱ ከገጠማት ውስብስብ ችግርና የውጭ ተጽዕኖ በማላቀቅ የጀመሩትን የዴሞክራሲ ስርዓት ማጠናከር እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል።

አሸናፊው ፓርቲም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች አቅም ያላቸውን ግለሰቦች ወደ ስልጣን በማምጣት ለሀገር አሻራችውን እንዲያስቀምጡ ቢያደረግ ሁላችንም እናተርፋለን  ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

በሌላ በኩል በምርጫው በማሸነፍ አዲስ የሚመሰረተው መንግስት የሀገሪቱን ዜጎች በእኩልነት ለማገልገልና የተጀመሩ ልማቶችን ለማስቀጠል ትኩረት እንዲሰጥ  በሀድያዞን ነዋሪዎች ጠይቀዋል።

በዞኑ አምቡርሴ ምርጫ ጣቢያ  የተለጠፈውን ጊዜያዊ የድምጽ ውጤት ዛሬ ሲመለከቱ ኢዜአ ያነጋገርናቸው ወይዘሮ ምህረት ዋዳ  በሰጡት አስተያየት በህዝብ ድምጽ ስልጣን የሚይዘው መንግሥት ዜጎችን ከድህንነት ለማላቀቅና ሀገሪቱን ካደጉት ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ ሊተጋ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ህዝቡም እንዲመራው ድምጹን ለሰጠው መንግሥት የሚጠበቅበትን ተሳትፎ በማድረግ የተሻለች ሀገር ለመገንባት ብርቱ ጥራት ልናደርግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ወጣት አበራሽ ኤራሞ በበኩሏ፤  በጊንቢቹ ምርጫ ጣቢያ ያመነችበትን ተወካይ ል በመምረጥ የዜግነት ግዴታዋን መወጣቷን ገልጻለች።

በምርጫው አሸናፊ የሆነው ፓርቲ ለወጣቶች ሰፊ የስራ እድል በማመቻቸት ለሀገሪቱ ልማትና እድገት መስራት እንደሚጠበቅበት ተናግራለች።

በአካባቢዋ የሚስተዋለው የመሰረተ ልማት ክፍተት ለማስተካከል ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት እንዲሰራ  ፍላጎቷ መሆኑንን ጠቅሳለች።

በሀገሪቱ የታቀዱ የልማት ስራዎች ስኬታማ የሚሆኑት ቅድሚያ ሠላማችንን ስናረጋግጥነው ያሉት ደግሞ በሾኔ ምርጫ ጣቢያ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ሞገስ ጡሜቦ ናቸው።

በምርጫው ለስልጣን የሚበቃው አካል የህዝብን ሰላም በማስጠበቅ ጠንክሮ ከሰራ ለውጥ የማያመጣበት ምክንያት የለም ብለዋል።

ህዝቡም ውጫዊና ውስጣዊ ጠላቶቹን በጋራ እየመከተ በልማቱ አዲስ ከሚመሰረተው መንግሥት ጎን በመቆም ለለውጥ መትጋት እንዳለበት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም