ቀጥታ፡

ለትውልዱ አረንጓዴና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማስረከብ ችግኝ ከመትከል ባለፈ ተንከባክቦ ማሳደግ እንደሚገበ ተገለጸ

አዲስ አበባ ሰኔ 16/2013 (ኢዜአ) ለአዲሱ ትውልድ አረንጓዴና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማስረከብ ችግኝ ከመትከል ባለፈ ተንከባክቦ ማሳደግ እንደሚገበ ተገለጸ።

የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ሠራተኞች "ኢትዮጵያን እናልብሳት" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ ችግኝ ተክለዋል። 

ዛሬ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የድርጅት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት ትልቁን ጨምሮ የተቋሙ ሠራተኞች ተገኝተዋል።

ዳይሬክተሯ በእዚህ ወቅት እንዳሉት ከሀገራዊ ምርጫው ማግስት ችግኝ ተከላ ማካሄዳቸው የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል ጠቀሜታው የጎላ ነው።

በዛሬው ዕለት ከ1 ሺህ በላይ ችግኞች መተከላቸውን ጠቁመው፣ የችግኝ ተከላው ለተከታታይ አምስት ቀናት እንደሚካሄድና በእነዚህ ቀናትም 10 ሺህ ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያን እናልብሳት" በሚል መርህ እየተካሄደ ባለው የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ በመሳተፋቸውም መደስታቸውን ነው የገለጹት።

የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ለአየር ብክለት ከሚጠቀሱ ምከንያቶች አንዱ መሆኑን ያመለከቱት ዳይሬክተሯ፣ በእዚህም ተቋሙ ችግኞችን በመትከል በኩል ድርብ ሃላፊነት እንዳለበት ነው ያመለከቱት፡፡

ለአዲሱ ትውልድ አረንጋዴና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማስረከብ ችግኝ ከመትከል ባለፈ በአግባቡ ተንከባክቦ ማሳደግ ይገባናል ብለዋል።

ታለቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብንም ሆነ ሌሎች ገድቦች ቀጣይነት ባለው መልኩ ውሃ እንዲያገኙና ከደለል እንዲጠበቁ የችግኝ ተከላ ስራውን ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ሠራተኛ የሆኑት አቶ አበበ ካፕትይመር በበኩላቸው፣ የሕዳሴው ግድብም ሆነ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያዊያንን ህብረት የሚያሳይ ነው

የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሰው እንዲያገግሙ ለማድረግና የአየር ንብረት ለውጥን ለማስተካከል የችግኝ ተከላ ስራው ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ነው የገለጹት

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ ጀምሮ ችግኝ በመትከል እንደሚሳተፉና በእዚህም ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ ሰይፉ ድሪባ የተባሉ ሌላው የተቋሙ ሠራተኛ ናቸው።

"ንጹህ፣ ያለተበከለና ነፋሻማ የአየር ነብረት እንዲኖር አረንጓዴ ልማትን ማጠናከር ይገባል" ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ከዚህ ቀደም ሠራተኞቹን በማስተባባር 39 ሺህ ችግኝ መትከሉ ተገልጿል፡፡

በዘንድሮው "ኢትዮጵያን እናልብሳት" የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአገር አቀፍ ደረጃ 6 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል።

በአዲስ አበባ ደግሞ ከ7 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዞ ወደ ተግባር ተገብቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም