ቀጥታ፡

አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ጋር ተወያዩ

ሰኔ 16/2013 (ኢዜአ) አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጄምስ ዋኒ ኢጋ ጋር በውቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ተወያዩ።

አምባሳደር ነቢል የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ረጅም ታሪክ ያስቆጠረና በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ መሆኑን በማውሳት፤ ይህንንም የሁለቱን አገራት ሕዝቦች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተጨባጭ የልማት ሥራዎች መደገፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ከዚህ አንጻር ሁለቱን አገራት በመንገድና በኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ-ልማት ለማስተሳሰር የተጀመረው ጥረት እንዲሳካ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ከዚህ ባሻገር ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር በጎረቤት ሀገራት ጭምር ለማስጀመር የያዘችውን ዕቅድ ለምክትል ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

በዚሁ መሠረት የፊታችን ሐምሌ 2 ከሚከበረው የደቡብ ሱዳን 10ኛ ዓመት የነጻነት በዓል ጎን ለጎን ችግኝ ተከላው አንድ አካል እንዲሆን ፍላጎት መኖሩን ተናግረዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱም የዕቅዱን ጠቀሜታና ወቅታዊነት በመግለጽ ለተግባራዊነቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጻዋል።

በተጨማሪ አምባሳደር ነቢል በሕዳሴ ግድብ ድርድር ሂደት፣ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ አስመልከቶ ገለጻ አድርገዋል።

እንዲሁም 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ያሸነፉበት ነጻና ሰላማዊና ምርጫ ሆኖ መጠናቀቁን ለምክትል ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዋኒ ኢጋ ኢትዮጵያዊያን ለደቡብ ሱዳን ነጻነት ከደቡብ ሱዳናዊያን ጎን የሕይወት መስዕዋትነት መክፈላቸውን በማስታወስ፣ ይህ ውለታ ሁሌም የማይዘነጋ መሆኑን ገልጸዋል።

የሁለቱን ሀገራት ግንኑኘት የበለጠ ለማጠናከር የመሠረተ-ልማት ትስስሮች ላይ ማተኮር ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።ዶ/ር ጄምስ ዋኒ 6ኛው አገራዊ ምርጫ በሰላም በመጠናቀቁ የተሰማቸውን ደስታም ገልጸዋል።

የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለደቡብ ሱዳንና ለአካባቢው ትልቅ ጸጋ መሆኑን ገልፀው፤ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የድንበር ውዝግብ በውይይት ብቻ መፍታት የሚገባው መሆኑን በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም