ምርጫ በተጠናቀቀባቸው አብዛኞቹ የምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ ቆጠራ ተጠናቋል- ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫ በተጠናቀቀባቸው አብዛኞቹ የምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ ቆጠራ ተጠናቋል- ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሰኔ 15/2013 ምርጫ በተጠናቀቀባቸው አብዛኞቹ የምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ ቆጠራ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ።
የቦርዱ ኮሙኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ፤ በምርጫ ሂደቱ ያለውን አጠቃላይ አንቅስቃሴ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ምርጫ በተጠናቀቀባቸው አብዛኞቹ የምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ ቆጠራ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ዛሬ ከሰዓት ጀምሮ ባሉት አምስት ቀናት የምርጫ ክልል ውጤት ይገለፃል ወደ ዋናው ማዕከል ገብቶ በአስር ቀናት ውስጥም ጊዜያዊ ውጤት ይገለፃል ብለዋል።
በትናንትናው እለት ድምፅ መስጠት ባልተጠናቀቀባቸው የሲዳማና ጋምቤላ ክልል ምርጫ ክልሎች ቁሳቁስ ተሟልቶ ድምጽ እየተሰጠ በመሆኑ ዛሬ ይጠናቀቃል ነው ያሉት።
በደቡብ ክልል 90 በመቶ እንዲሁም በአዲስ አበባ በአብዛኛው የምርጫ ጣቢዎች ቆጠራ ተጠናቋል ብለዋል።
ቦርዱ ውጤት ሳይገልጽ ከምርጫ ጣቢያ ውጤት በመነሳት "እከሌ አሸነፈ" የሚል መረጃ የሚለቁ በተለይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተከታይ ያላቸው አክቲቪስቶች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።