ቀጥታ፡

የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ያልተጠናቀቀባቸው ቦታዎች ላይ ሂደቱ ዛሬ እንደሚከናወን ቦርዱ አስታወቀ

ሀዋሳ፣ ሰኔ 15 ቀን 2013 (ኢዜአ) በትናንትናው እለት የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ያልተጠናቀቀባቸው ቦታዎች ላይ የድምጽ መስጠት ሂደት ዛሬ እንደሚከናወን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

ቦርዱ ባወጣው መግለጫ 6ተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በትላንትናው እለት በሰላም እንደተጠናቀቀ አስታውሷል።

በዛሬው እለት ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የተጠናቀቁ የድምፅ ቆጠራ ውጤቶች ይፋ እየሆኑ እንደሚገኝ ገልጾ፤ “በትናንትናው እለት የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ሳይጠናቀቅ በቀረባቸው ቦታዎችም በተመሳሳይ የድምፅ መስጠት ሂደት ዛሬ የሚከናወን ይሆናል” ብሏል።

በዚህም መሰረት በሲዳማ ክልል በሁሉም ምርጫ ክልሎች ከረፋዱ 5 ሰአት ጀምሮ የድምጽ አሰጣጡ ሂደት የቀጠለ ሲሆን በዛሬው እለት እንደሚጠናቀቅ አስታውቋል።

በጋምቤላ ክልል ባሉ የተወሰኑ የምርጫ ክልሎች ተቋርጦ የነበረው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ዛሬ ከቀኑ 8 ሰአት ጀምሮ ቀጥሎ በዛሬው እለት እንደሚጠናቀቅ ገልጿል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሁለት ምርጫ ክልሎች ያለው ድምጽ አሰጣጥ ሂደት ለጊዜው መቆሙን ገልጾ፤ ቁሳቁሶች በሙሉ ታሽገው እንዲጠበቁ ቦርዱ ለአስፈጻሚዎች አስታውቋል።

“በዚህም መሰረት ቦርዱ የሚቀጥለው የድምፅ አሰጣጥ ሁኔታ እና እስካሁን ያለውን ሂደት ገምግሞ ውሳኔ ላይ ደርሶ የሚያሳውቅ ይሆናል” ሲል ቦርዱ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም