በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምርጫው ያለምንም የፀጥታ ችግር መጠናቀቁን ፖሊስ ተገለጸ

አዲስ አበባ ሰኔ 15/2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሲካሄድ የነበረው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም መጠናቀቁን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ተወካይ ኮማንደር ብዙነህ አጎናፍር ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የምርጫው ሂደት ፍፁም ሰላመዊ በሆነ መልኩ መከናወኑን ገልጸዋል።

በዞኑ ድምጽ መስጠት ከተጀመረበት ከትናት ጧት 12 ሰዓት ጀምሮ ችግር እንዳልገጠመም ተናግረዋል።

በዞኑ ድምጽ የተሰጠባቸው 13 የምርጫ ክልልና 1 ሺህ 128 የምርጫ ጣቢያዎች ህዝቡ በሰላምና በተረጋጋ መልኩ ድምጽ ሲሰጥ መዋሉን አብራርተዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ግን ከምርጫ ስነ-ምግባር ውጭ የሆኑ እንቅስቃሴዎች መስተዋላቸውን አንስተዋል።

ከዚህ ውጪ የህብረተሰቡን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥልና የተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ የሚገድብ ችግር አለመከሰቱን ጠቁመዋል።

በዞኑ በየምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ውጤት እየተለጠፈ ሲሆን የምርጫ ሳጥኖችም በፀጥታ አካላት ታጅበው ወደ ሚመለከተው ክፍል እየተጓዘ መሆኑን ተናግረዋል።

ከምርጫ ውጤት በኋላ የተፎካካሪ ፓርቲዎች የህዝብን ድምጽ በማክበርና ውጤቱ በጸጋ በመቀበል እንዲቀሳቀሱ ፖሊስ መምሪያው ጥሪ አቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም