ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ስነ-ምግባር ባከበረና ከፍ ባለ አገራዊ ስሜት ለሰሩት ዘገባ ምስጋና ይገባቸዋል - የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን

አዲስ አበባ፣  ሰኔ 14 ቀን 2013 (ኢዜአ) መገናኛ ብዙሃን የምርጫውን ሂደት ሙያዊ ስነ-ምግባር ባከበረና ከፍባለ አገራዊ ስሜት መዘገባቸው የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ገለጸ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሀመድ ኢድሪስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መገናኛ ብዙሃን በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ግልጽ፣ ፍትሃዊ፣ ሙያዊ ስነ-ምግባርና መመሪያን የተከተሉ ዘገባዎችን ሲሰሩ ውለዋል።

ጋዜጠኞች መረጃዎችን ለማሰባሰብ በከተማና በገጠር አካባቢዎች ተሰማርተው በተቀናጀ መልኩ ሚዛናዊና ትክክለኛ  ዘገባዎችን አቅርበዋል ብለዋል።

"ይህም ጋዜጠኞች መስዋዕትነት ጭምር ለመክፍል ያላቸውን ዝግጁነት ያሳያል" ሲሉ ነው የገለጹት።

ዘገባዎችን ለሕዝብ ተደራሽ ሲያደርጉ በላቀ አገራዊ ስሜት እንደሆነ ያስታወሱት ዋና ዳይሬከተሩ፤ ይህ ተግባራቸው በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል መሆኑን አብራርተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ መገናኛ ብዙሃኑ በአገራዊ ምርጫው ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።

በተመሳሳይ ምርጫውን ለመዘገብ የገቡ የውጭ መገናኛ ብዙሃንም እስካሁን ባለው ሂደት የምርጫውን ዴሞክራሲያዊ ሂደትና ትክክለኛነት የሚያሳዩ መረጃዎችን ለዓለም ሕዝብ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

በአንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን በምርጫው አዘጋገብ ላይ የተወሰኑ ችግሮች ቢስተዋልባቸው በአብዛኛው ግን በመልካም ሊጠቀስ የሚችልና የምርጫ ሂደቱን እውነታ ያሳየ እንደነበር አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም