ቀጥታ፡

ቦርዱ የምርጫ ውጤት እስከሚገልጽ ድረስ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ መግለጫ ከመስጠት ሊታቀብ ይገባል ... የጋራ ምክር ቤቱ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 14/2013(ኢዜአ) የፖለቲካ ፓርቲዎች የድምፅ መስጠት ሂደት እና ቆጠራ ተጠናቆ በቦርዱ ውጤት እስከሚገለፅ ድረስ መግለጫ ከመስጠት እንዲታቀቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አሳሰበ።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ይህን ያስታወቀው ምርጫውን አስመልክቶ  ማምሻውን በሰጠው መግለጫ ነው።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ዶክተር ራሄል ባፌ  በምርጫው የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ህጉ ተገዢ እንዲሆኑ አሳስበዋል።

በምርጫው ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ ሽግግር መሰረት እየጣለች መሆኑን ምክር ቤቱ እንደሚገነዘብ በማንሳት፤ በሂደቱ የሚፈጠሩ ችግሮች ካሉ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፈታት እንዳለባቸው ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ  መንግስት ሀገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓርቲዎች ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ወቅታዊና ተገቢ ምላሽ እንዲሰጥ መልዕክት አስተላልፈዋል።

መንግስት ሰላምና ጸጥታ የማረጋገጡን ኃላፊነት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።    

ፓርቲዎች የድምፅ መስጠት ሂደት እና ቆጠራ ተጠናቆ በቦርዱ ውጤት እስከሚገለፅ ድረስ መግለጫ ከመስጠት እንዲታቀቡም  የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ዶክተር ራሔል ባፌ አሳስበዋል።።

መላው የአገሪቱ ህዝቦች በተረጋጋ መንፈስ ለአገሪቱ ደህንነትና ሰላም በአንድነት እንዲቆሙም ሰብሳቢዋ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም