በደብረ ማርቆስ ከተማ እየተካሄደ ባለው የድምጽ አሰጣጥ ላይ የጎላ ችግር አላየንም --ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
በደብረ ማርቆስ ከተማ እየተካሄደ ባለው የድምጽ አሰጣጥ ላይ የጎላ ችግር አላየንም --ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች
ደብረማርቆስ ሰኔ 14/2013 ( ኢዜአ) በደብረ ማርቆስ ከተማ እየተካሄደ ያለው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና በህዝብ ዘንድ ተአማኒ ሆኖ መቀጠሉን ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ገለጹ።
ተወካዮቹ በደብረ ማርቆስ ከተማ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የብልጽግና ፓርቲን የወከሉት የደብረ ማርቆስ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ይትባረክ አወቀ እንዳሉት ከባለፉት ምርጫዎች በመማር ምርጫውን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ በሃላፊነት ተሰርቷል።
በዚህም ህዝቡ የኔ ድምጽ አገሬን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሻገር ዋጋ አላት ብሎ በነቂስ በመውጣት ሰልፍ ሳይበግረው መምረጡን ገልጸዋል።
“ይህም ምርጫው በህዝብ ዘንድ ተአማኒ እንዲሆንና ሰላማዊ በማድረግ ህዝብ ባመነበት ጉዳይ ወደ ኋላ እንደማይል የተረዳሁበት ነው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ/ኢዜማ/ ተወካይ አቶ ሰሎሞን ጉልበት በበኩላቸው ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ማድረግ የውጭና የውስጥ ጠላቶችን ሴራ ማክሸፍ ነው።
በዚህም ከውሃ አጠቃቀም፣ጎረቤቶቻችን ካሉበት ሁኔታና የቀድሞው ስርዓት ርዝራዦች እየፈጠሩ ካሉት ችግር ተያይዞ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድነት እንዲቆሙ ፓርቲያቸው እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ በማጠናቀቅም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ከህዝብና ከመንግስት ጎን ለመሰለፍ ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት/መኢአድ/ ተወካይ አቶ ብርሃኑ ማናየ እንዳሉት በምርጫው ዘግይቶ ከመጀመርና ከተወሰኑ ጥቃቅን ችግሮች ውጭ ምርጫው ሰላማዊ ነው።
“እነዚህን ችግሮችም ከምርጫ ማስተባበሪያውና ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመነጋገር ወዲያው በመፍታት ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን ተደርጓል” ብለዋል።
ከሰዓት በፊት 18 የምርጫ ጣቢያዎችን ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን ጠቁመው ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ፓርቲ በነጻነት እየመረጠ መሆኑን መገንዘባቸውንም አስገንዝበዋል።
ምርጫው እስከ ፍጻሜው በዚሁ መንገድ ከቀጠለ ዴሞክራሲያዊና በህዝብ ዘንድ ተአማኒ ሆኖ የሚጠናቀቅበት እንደሚሆንም ተናግረዋል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን የሚወዳደሩ ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸውን ከምርጫ ማስተባበሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።