አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና እያሳደሩ ነው - የኢትዮጵያ ማኅበራት - ኢዜአ አማርኛ
አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና እያሳደሩ ነው - የኢትዮጵያ ማኅበራት
ሰኔ 14/2013 (ኢዜአ) አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት የትግራይን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ የያዙት አቋም ተገቢ አለመሆኑን በአውሮፓና አሜሪካ የሚንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ገለጸ።
ማኅበራቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ እነዚህ መንግሥታዊ ያልሆኑ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ትግራይን በተመለከተ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እያሳደሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በቀጣይ በሚካሄደው የተ.መ.ድ የሰብዓዊ መብት ካውንስል 47ኛ መደበኛ ስብሰባ በኢትዮጵያ ላይ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ግፊት እያደረጉ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።
በትግራይ የሕግ ማስከበር ሥራውን ተከትሎ የተከሰተው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ማኅበሩ እንደሚያወግዝ አመልክተው፤ መንግሥት አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቅሷል።
ኢትዮጵያም ሉዓላዊ አገር እንደመሆኗ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የፈጸሙ አካላትን አግባብ ባለው የፍትህ ሥርዓት በፍጥነት ተጠያቂ እንደምትደርግ እምነት እንዳላቸው ተመላክቷል።
መንግሥት ይህንን ጉዳይ በጥቂት ኃብት በማይመች ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን ማኅበሩ ጠቁሟል።
ያም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን በጋራ እየሰሩ መሆኑ ነው ማህበሩ ባወጣው መግለጫ ያሳወቀው።
በሁለቱ ተቋማት የሚካሄደው ምርመራ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እንደሆነ ያመለከተው የማህበሩ መግለጫ፤ በቅርቡ የተደረሰበት ውጤት ይፋ ይደረጋል ብለው ማኅበራቱ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጥፋተኛ ባላቸው የሕውሃትና ጥቂጥ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ የመሰረተው ክስ ፍትህን ለማረጋገጥ የያዘውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑም ተብራርቷል።
በአንዳንዶቹ አባላት ላይ ደግሞ ውሳኔ መተላለፉን መግለጫው አስታውሷል።
ይህ ሁሉ ተጨባጭ ማስረጃ መንግሥት ለጉዳዩ የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ነው ያለው መግለጫው፤ ከዚህ ተቃራኒ የሚደረገው ግፊት ጥረቱን መና የሚያስቀር ነው ብሏል።
ተቋማቱ የሚያደርጉት ግፊት ያልተረጋገጠና መሰረተ ቢስ ክስ ለማቅረብ በውሸት ማስረጃ የታጀበ ሲሆን፤ መሬት ላይ ያለውን እውነታ የካደ መሆኑ ሊታወቅ እንደሚገባ ጠቅሷል።
ተቋማቱ የሚያደርጉት ግፊት ጥረቱ የህወሃት ርዝራዦች የሀሰት መረጃን መሰረት ያደረገና የፖለቲካ የበላይነትን ለማግኘት የፈጠሩትን ውሸትን ያካተተ ነው ይላል መግለጫው።
በትግራይ የሚኖሩ ህዝቦቻችን ከገጠማቸው ችግር እንዲወጡ ድርጅቶቹ አስቸኳይ ድጋፍ በማድረግ የተጎዱትን መታደግ እንደሚገባቸው ተገልጿል።
ከዚህ ባለፈ ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዟን ለማሻሻል የምታደርገውን ተቋማዊ ሽግግር ከግምት ማስገባት አስፈላጊ መሆኑን ነው የተጠቀሰው።
ይሁንና ከዚህ በተቃራኒ ያልተገባ ክስ ውስጥ መግባታቸው ለማንም እንደማይጠቅም ነው በመግለጫው የተጠቆመው፡፡
የማህበሩ መግለጫ እንደሚያትተው፤ በተጨማሪም ይህ ተግባር በኢትዮጵያና በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ካውንስል መካከል ያለውን ውጤታማ ትብብር የሚያደናቅፍ ነው።
ስለሆነም ማኅበራቱ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ካውንስል አባል አገሮች በጋራ እየተደረገ ያለውን ምርመራ እንዲደግፉ ማህበሩ ጥሪ አቅርቧል።
ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግስት ተጠያቂነትን በማስፈን በትግራይና በተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት እንዲደግፉ ማህበሩ ጠይቋል።