ቀጥታ፡

ያለ ልዩነት በጋራ በመስራት ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንሰራለን -የፖለቲካ ፓርቲዎች

ሀዋሳ፣ ሰኔ 14 /2013 (ኢዜአ) እንደ ችግኝ ተከላው ያለ ልዩነት በጋራ በመስራት ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንሰራለን ሲሉ በሀዋሳ ድምጽ የሰጡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ።

በሀዋሳ ድምጽ የሰጡ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች በጋራ ችግኝ ተክለዋል። 

በሲዳማ ክልል የብልጽግና ፓርቲን ወክለው የሚወዳደሩት አቶ ደስታ ሌዳሞ ከችግኝ ተከላ በኋላ እንዳሉት በአንድ እጅ ምርጫ በሌላ እጅ ችግኝ በመትከል ሀገራችን የጀመረችውን የልማት ጉዞ ለማስቀጠል እንሰራለን።

"ምርጫ ቦርድ የመጨረሻውን ውጤት ይፋ በሚያደርግበት ጊዜም ውጤቱን በጸጋ ከመቀበል ባለፈ ለልማት ቁርጠኛ በመሆን እንደ ችግኝ ተከላው በጋራ ሰርተን ለውጥ እናመጣለን" ብለዋል።

ዛሬ የተተከሉት ችግኞች ለ7ኛው ምርጫ እንዲጸድቁ በተገቢው መንገድ እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እጩ አቶ ፋንታሁን ሀጢሶ በበኩላቸው "ዴሞክራሲ ከየት ወዴት እየሄደ እንደሆነ አንዱ ማሳያና መገለጫ ከምርጫው በኋላ በጋራ ችግኝ በመትከል ያሳረፍነው አረንጓዴ አሻራ ማሳያ ነው" ብለዋል።

"በቀደመው ጊዜ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለልተኞች ነበርን፤ አሁን ግን አብረን እንመርጣለን፤ አብረን ችግኝ እንተክላለን፤ ይህ ደግሞ በዕውቀት የሚመራ ፖለቲካ ስርዓት ላይ ነው ያለነው ማለት ነው"  ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

"ኢትዮጵያዊያን አንድ ላይ ሆነን በጋራ ከሰራን ወደ አለምነው ደረጃ ለመድረስ ምንም የሚያግደን ነገር የለም" ያሉት አቶ ፋንታሁን "ምርጫው ሰላማዊና ታአማኒነት ያለው እንዲሆን ሲባል ህዝብ የሚሰጠንን ድምጽ በጸጋ ተቀብለን ለአሸናፊው አካል እንኳን ደስ ያለህ መልዕክት በማስተላለፍ በቀጣይ ለመፎካከር እንሰራለን" ሲሉም ተናግረዋል።

"ሁከት መፍጠር ለሀገራችን ሰላምና ለፖለቲካው ጥሩ ስላልሆነ ከውስጥም ከውጪም ያሉ ጸረ ኢትዮጵያ አካላትን ማሳፈር የሁላችንም ሀላፊነት ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም