ቀጥታ፡

በምርጫ ሂደቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋነቱንና ሕግ አክባሪነቱን እያሳየ ነው - መራጮች

አዲስ አበባ ሰኔ 14 ቀን 2013 (ኢዜአ) በመካሄድ ላይ የሚገኘው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋነቱንና ሕግ አክባሪነቱን በተግባር እያሳየ መሆኑን መራጮች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋና አንጋፋው የጥበብ ሰው አርቲስት ደበበ እሽቱ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ምርጫ ጣቢያ 10 እና 11 በመገኘት ድምጽ ሰጥተዋል።

አቶ የሺዋስ የዘንድሮ ምርጫ ያማረ ድባብ ተላብሶ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ምርጫውን ለማድረግ ብዙ ውጣ ውረዶች እንደነበሩ ጠቅሰው ሁሉም ነገሮች አልፈው በተሻለ ሁኔታ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ወደፊትም ምንም ነገር ቢፈጠር ዜጎች ከአገራቸውና ከሕዝባቸው ጎን ሆነው የምርጫው ውጤት መልካም እንዲሆን መደረግ አለበት ብለዋል።

የምርጫው ውጤት ምንም ይሁን ምን ፓርቲያቸው የሕዝቡን ዳኝነት ለመቀበል ዝግጁ መሆኑንና ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችም ይህንን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የሰባተኛ ክፍል ተማሪው ታዳጊ ከአባቱ ጋር ስለ አገሩ ፖለቲካ እንደሚያወራ ገልጾ፣ ዛሬም በምርጫ ጣቢያ መገኘቱ ብዙ ጥቅም እንደሚሰጠው ተናግሯል።

አንጋፋው የጥበብ ሰው አርቲስት ደበበ እሸቱ በበኩሉ ከዚህ በፊት የነበሩት ምርጫዎች የ'ይስሙላ' ምርጫዎች ነበሩ ይላል።

በዚህኛው ምርጫ አስተባባሪዎቹ ጭምር ሥርዓት ባለው መልኩ መራጮችን ተቀብለው ሲያስተናግዱ ተመልክቻለሁ ብሏል።

የፖለቲካ ድርጅቶች ''የሰጠናቸውን ድምጽ መልካም በመስራት ይክሱናል ብዬ አምናለሁ'' ሲል ተስፋውንም ገልፇል።

''ከዚህ በኋላ የተጀመረውን እድገት ማስቀጠል አለብን፤ በአጠቃላይ ለአገሪቷና ለሕዝቡ የተገባው ቃል መፈጸም አለበት'' ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም