ቀጥታ፡

ምርጫው በሁሉም አካባቢዎች በሰላማዊ መንገድ እየተከናወነ ነው- ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ

 አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሰኔ 14/2013 ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው ጠቅላላ ምርጫ በሁሉም አካባቢዎች በሰላማዊ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ገለጹ።

የቦርዱ ሰብሳቢ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ምርጫ በሚካሄድባቸው ሁሉም አካባቢዎች የድምፅ አሰጣጡ በሰላማዊ መንገድ እየተከናወነ ነው።

በአብዛኞቹ ምርጫ ጣቢያዎች በሰዓቱ ጀምረው ምርጫውን እያከናወኑ መሆኑንም ገልፀዋል።

በአዲስ አበባ ዘጠኝ ምርጫ ጣቢያዎች "ሃላፊነት የጎደላቸው" ምርጫ አስፈፃሚዎች በቦታው ሳይገኙ መቅረታቸውን ጠቅሰዋል።

ሆኖም ሌሎች 27 አስፈፃሚዎችን ቃለ መሃላ በማስፈፀም ስራ እንዲጀምሩ በመደረጉ የምርጫ ሂደቱ ዘግይቶ ተጀምሯል ብለዋል።


በተመሳሳይ በአዲስ አበባ አንድ የምርጫ ጣቢያ መዝገብ ጠፎቶ መራጮች ያወጡት ካርድ እየታየ እንዲመርጡ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፣ ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑን ተገናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል አምቦ አንድ የምርጫ ጣቢያ ምንም ሳይፈጠር የተደናገጡ ምርጫ አስፈፃሚዎች ቦታውን ለቀው ቢሸሹም የተፈጠረ ችግር ባለመኖሩ ድምፅ የመስጠት ሂደቱ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።


ከምርጫው ጋር በተያያዘ በአማራና ደቡብ ክልሎች በፖርቲ ተወካዮች ላይ ማስፈራራት አለ በሚል ለደረሰን ጥቆማ ችግሩን በአፋጣኝ ለመፍታት ከክልል አስተዳደሮች ጋር ተነጋግርናል ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችና እጩዎችን ተሳትፎና ተዘዋውሮ የመታዘብ መብት መገደብ የተከለከለና በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑንም ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም