ለሀገርና ለህዝብ ይበጀልና ያስተዳድረናል ብለን ያመንበትን በነጻነት መርጠናል --- የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገርና ለህዝብ ይበጀልና ያስተዳድረናል ብለን ያመንበትን በነጻነት መርጠናል --- የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች
ደብረማርቆስ ሰኔ 14/2013 (ኢዜአ) የመምረጥ መብታችን ተጠቅመን ለሀገርና ለህዝብ ይበጀል ያስተዳድረናል ብለን ያመንበትን በነጻነት መርጠናል ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ገለጹ።
ከድምጽ ሰጪዎች መካከል በከተማዋ የቀበሌ 03 ነዋሪ የሆኑት አቶ መንግስት መኮነን እንደገለጹት ከጧቱ 12 ሰዓት ወደ ምርጫ ጣቢያ-2 መጥተው በመሰለፍ ከአንድ ሰዓት ተኩል በኋላ ወረፋ እንደደረሳቸው ተናግረዋል።
ወረፋ እንደደረሳቸውም ወደ ድምጽ መስጫ ጣቢያው በመግባት ያለምንም ተጽእኖ በነጻነት ድምጻቸውን ሰጥተው መውጣታቸውን ገልጸዋል።
"እንደ ዘንድሮው ምርጫ ያለ መራጩ ህብረተሰብ በነጻነት የሚመርጥበት እድል የከፈተ የተለየ ምርጫ ከአጼ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ አላየሁም" ያሉት ድምጽ ሰጪው በምርጫው ማንም ያሸንፍ ሃገርን ቅድሚያ በመስጠት በጋራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በደብረ ማርቆስ ከተማ ቀበሌ 05 ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ፋሲካ ሙሉየ በበኩላቸው ልጆቻቸው ገና ሳይነሱ በጧቱ ወደ ምርጫ ጣቢያው መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ሰልፉ በመብዛቱ ወረፋ ለመጠበቅ መገደዳቸውን ገልጸው “አገርና ህዝብን ወደ ተሻለ ደረጃ ያሻግራል የምለውን ፓርቲ በነጻነት መርጫለሁ” ብለዋል።
በድምጽ መስጫ ቦታው በአስፈጻሚዎች የአመራረጥ ሂደቱን አስመልክቶ ትምህርት መሰጠቱና አቅመ ደካሞችንና ነፍሰ ጡሮችን በማስቀደም በኩል መስተንግዶው መልካም መሆኑንም አስረድተዋል።
እርሳቸው ድምጽ በሰጡበት ቀበሌ 05ምርጫ ጣቢያ አራት ከ1ሺህ 111 በላይ መራጮች ካርድ ወስደው በዛሬው እለት ድምጽ እየሰጡ መሆናቸውን ከጣቢያው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ፓርቲዎች በሚዲያ፣ በአደባባይና በአዳራሽ ጭምር ፖሊሲዎቻቸውንና ፕሮግራማቸውን ማስተዋወቃቸው ቀድሞ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማስቻሉ በምርጫው ለመወሰን እንዳልተቸገሩ አስተያየት ሰጪዎቹ አስረድተዋል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን በ1ሺህ 451 የምርጫ ጣቢያዎች ከ856ሺህ 100 በላይ ካርድ ያወጣ ህዝብ ዛሬ ከጧቱ 12 ጀምሮ ድምጽ እየሰጠ መሆኑ ተመልክቷል።