የጋምቤላና የአምቦ ነዋሪዎች ድምፃቸውን እየሰጡ ነው

57

አዲስ አበባ /ጋምቤላ ሰኔ 14 ቀን 2013 (ኢዜአ)በጋምቤላና  በአምቦ ከተማ ማለዳ ላይ የተጀመረው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት እየተከናወነ ነው።

የከተማዋ ከንቲባ፣ የአምቦ ቁጥር አንድ ምርጫ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ አቶ ሣህሉ ድሪብሣና በርካታ ነዋሪዎች ከማለዳው 12 ሠዓት ጀምሮ በየምርጫ ጣቢያዎች ድምጻቸውን በመስጠት ላይ ናቸው፡፡


በአምቦ ቁጥር አንድ የምርጫ ክልል 94 የምርጫ ጣቢያዎች ይገኛሉ።


በተጠቀሱት ጣቢያዎችም 69 ሺህ 696 መራጮች ተመዝግበዋል በርካቶችም ድምፃቸወን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።


የኢዜአ ሪፖርተር በአምቦ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱን በአራት የምርጫ ጣቢያዎች እንደተመለከተው በምርጫ ጣቢያዎቹ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ በተረጋጋ ሁኔታ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በኦሮሚያ ክልል ለሕዝብ ተወካዮችና ለክልል ምክር ቤቶች ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች 906 ዕጩዎችን አቅርበዋል።

በክልሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች 268 ዕጩዎች ያቀረቡ ሲሆን 78ቱ ሴቶች ናቸው።

የአካል ጉዳት ያለባቸው ሁለት ተወዳዳሪዎች ተካተዋል፤ 11 የግል ዕጩዎችም ቀርበዋል።

ለክልል ምክር ቤት ከቀረቡት 638 ዕጩዎች መካከል 249 ሴቶች ሲሆኑ፤ ከእነዚህ መካከል ሶስት የአካል ጉዳት ያለባቸው እንዲሁም አራት የግል ተወዳዳሪዎች ይገኙበታል።

በተመሳሳይ በጋምቤላ ክልል  ኚንኛንግ ከተማ  በመራጭነት የተመዘገቡ ነዋሪዎች ድምጻቸውን እየሰጡ ነው።

በስፍራው የሚገኘው የኢዜአ ሪፖርተር እንደተመለከተው ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ታዛቢዎች በተገኙበት ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ በኋላ ነዋሪው ተሰልፎ  እየመረጠ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም