ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ምርጫ ጣቢያዎች ለነገ ድምፅ አሰጣጥ ዝግጁ ሆነዋል

ሰኔ 13/2013 (ኢዜአ)) የአዲስ አበባ ምርጫ ጣቢያዎች ነገ ከማለዳው ጀምሮ ለሚካሄደው ድምጽ አሰጣጥ ዝግጁ ሆነዋል፤ የመዲናዋ ነዋሪዎችም ድምፃቸው ከመስጠት የሚያግዳቸው ስጋት እንደሌለባቸው ገልፀዋል።

በመዲናዋ ስድስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ አብዛኞቹ ዝግጅቶች በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በተዘዋወረባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ለድምፅ አሰጣጡ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች እየተሰራጩ ነው፤ የድንኳን ተከላ ስራም በአብዛኛው ተከናውኗል።

በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ነገ ማልደው በመገኘት ድምጻቸውን ለመስጠትና ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን ለማሳረፍ ተዘጋጅተናል ብለዋል።      

አስተያየት ሰጪዎቹ ድምጽ ከመስጠት የሚያግዳቸው ምንም አይነት ስጋት እንደሌለና በከተማዋ ያለው እንቅስቃሴም ሠላማዊ መሆኑን ነው የገለጹት።

የምርጫ ተፎካካሪዎችን ክርክሮች በመገናኛ ብዙሃን ሲከታተሉ መቆየታቸውን የገለጹት አቶ ዘለቀ ሹምቡሬ ፓርቲዎች የምርጫውን ውጤት በጸጋ በመቀበል ለዴሞክራሲ ግንባታ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጠይቀዋል።

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ መሰረት ጆቴ መራጮች ከምርጫ ጎን ለጎን ችግኝ በመትከል አሻራቸውን ማሳረፍ እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል።      

በአገሪቷ በተለያዩ ምርጫዎች መሳተፋቸውን የሚያስታውሱት አቶ መሃመድ ሁሴን የሚፈልጉትን ፓርቲ በካርዳቸው ወደ ስልጣን ለማምጣት እንደተዘጋጁ ገልጸዋል።

የከተማዋ ጸጥታ አስተማማኝ መሆኑንና ምርጫ እንዳይካሄድ ስጋት የሚያጭር ነገር እንደሌለም ተናግረዋል።

የምርጫ ካርድ የወሰዱ ዜጎች ያስተዳድረኛል የሚሉትን ፓርቲ በአግባቡ ሊመርጡ ይገባልም ብለዋል።

በከተማዋ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 3 የምርጫ ክልሎች የቁሳቁስ ስርጭት ስራውን የቃኘው የኢዜአ ሪፖርተር የምርጫ ክልል 23 አስተባባሪ አቶ መስፍን አዱኛን አነጋግሯል።

አስተባባሪው በምርጫ ክልሉ 76 የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በ76ቱ የምርጫ ጣቢያዎች የቁሳቁስ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ መካሄዱንም ተናግረዋል።

የክፍለ ከተማው 71 የምርጫ ጣቢያዎች ባሉት ምርጫ ክልል 20 የምርጫ ቁሳቁስ ከትናንትና ጀምሮ መከፈፈሉ ተገልጿል።

በቂርቆስ ክፍለ ከተማም በተመሳሳይ የምርጫ ቁሳቁስ ተሰራጭቷል፤ በክፍለ ከተማው 3 የምርጫ ክልሎች ያሉ ሲሆን ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 97 እጩዎች ለሰባት ወንበር ይወዳደራሉ።  

በክፍለ ከተማው ምርጫ ክልል 15 ውስጥ 36 የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸውን የምርጫ አስፈጻሚው አቶ ደበበ ለማ ተናግረዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም