በድሬዳዋ ለምርጫው ስኬታማነት አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ ለምርጫው ስኬታማነት አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል
ድሬዳዋ ሰኔ 13/2013 (ኢዜአ) በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ነገ የሚካሄደው 6ተኛው አገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ አስታወቀ።
የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዚያድ ያሲን ዛሬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ ለምርጫው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች በገጠርና በከተማ ወደ ተዘጋጁት 259 የምርጫ ጣቢያዎች ሙሉ በሙሉ ተሰራጭተዋል።
እነዚህን ቁሶች በመቆጣጠር ደህንነታቸውን በመጠበቅ በኩል የአስተዳደሩ ፖሊስ ኃላፊነቱን መወጣቱን ገልጸው ፖሊሶች የድምጽ መስጠት ሂደቱን ሰላማዊ ለማድረግ መሰማራታቸውንም ተናግረዋል።
ሃላፊው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳስታወቁት የምርጫ ካርድ የወሰዱ ዜጎች ለሚፈልጉት ፓርቲ ድምጻቸውን በመስጠት አገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማሸጋገር ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡
የድሬዳዋ 07 እና 09 ቀበሌ የምርጫ አስተባባሪ ሃላፊ አቶ ግርማ በየነ በበኩላቸው “በቀበሌዎች ለሚገኙ 40 የምርጫ ጣቢያዎች አስፈላጊው ቁሳቁስ ተሟልቶ ለነገው ምርጫ ዝግጁ ተደርጓል” ብለዋል፡፡
“የዘንድሮ ምርጫ በሁሉም ረገድ ሰላማዊና ነጻ ሆኖ እንዲከናወን የተደረገው ጥረት አበረታችና አስደሳች በመሆኑ ተአማኒነቱ የጎላ ይሆናል” ብለዋል፡፡
በመሆኑም ህዝቡ የወሰደውን ካርድ በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ ትላንት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ እንዳረጋገጡት በ259 የገጠርና የከተማ ምርጫ ጣቢያዎች አስፈላጊው የፖሊስ ኃይል ተመድቦ ለምርጫው ስኬታማነት እየተሰራ ይገኛል፡፡
የኢዜአ ሪፖርተሮች በከተማው ተዘዋውረው እንደተመለከቱት የድምጽ መስጫ ድንኳኖች እየተተከሉ ይገኛሉ፤ ወደ እያንዳንዱ ድምጽ መስጫ ስፍራ ችግኞችም እየተሰራጩ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡