በጋምቤላ ክልል ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ የጸጥታ ጥበቃ ስራ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ የጸጥታ ጥበቃ ስራ እየተካሄደ ነው
ጋምቤላ፣ ሰኔ 13/2013 (ኢዜአ) ነገ የሚካሄደው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በጋምቤላ ክልል ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው የጸጥታ ጥበቃ ስራ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ከ414 ሺህ 950 በላይ መራጮች ተመዝግበው ካርድ መውሰዳቸው ተመልክቷል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ቶማስ ቱት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ነገ የሚካሄደው ምርጫ ያለአንዳች የጸጥታ ስጋት ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከፌደራል ጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የተጠናከረ የጸጥታ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ ነው።
ክልሉ ከኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች እንዲሁም ደቡብ ሱዳን ጋር ሰፊ የወሰንና የድንበር ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቁጥጥሩን በማጥበቅ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
በተለይም ከኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች አጎራባች ዞኖች ጋር የተቀናጀ የጸጥታ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የምርጫ ድምጽ መስጫ ቁሳቁሶች ከጋምቤላ ከተማ ጀምሮ እስከ ምርጫ ጣቢያ ማድረስ ብቻ ሳይሆን በምርጫ ጣቢያዎችም ላይ አስፈላጊው ጥበቃ እየተደረገ መሆኑንም አቶ ቶማስ አስታውቀዋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ አቡላ ኡቦንግ በበኩላቸው፤ ነገ የሚካሄደው ሀገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቅ የተለያዩ አደረጃጀቶች በመፍጠር የተጠናከር የጸጥታ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የጥበቃ ስራውን በተቀናጀ አግባብ ለመምራት እንዲቻል ክልሉን በአራት ክላስተር በማደረጃት አስፈላጊውን የጸጥታ ኃይል የማሰማራት፣ የመከታተልና የመቆጣጠር ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በጋምቤላ ክልል በ14 የምርጫ ክልሎች ስር 423 የምርጫ ጣቢያዎች የተመገቡ ሲሆን ከ414 ሺህ 950 በላይ መራጮች ካርድ መውሰዳቸውን ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።