ቀጥታ፡

የአዊ ዞን ከመተከል ዞን ጋር በሚዋሰኑ የምርጫ ጣቢያዎቹ የተቀናጀ የፀጥታ ስራ እያከናወነ መሆኑን ገለጸ

ቻግኒ፣ ሰኔ 13 ቀን 2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የአዊ ዞን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን አዋሳኝ ምርጫ ጣቢያዎች የፀጥታ ችግር እንዳያጋጥም የተቀናጀ ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን አስታወቀ።

ከመተከል ዞን ጋር የሚዋሰኑ የአዊ ዞን ጓንጓ ወረዳ ምርጫ ጣቢያዎች የጸጥታ ችግር እንዳይገጥማቸው የተቀናጀ ተግባር እየተከናወነ ተጠቁሟል።

የወረዳው ፖሊስ ፅህፈት ቤት አዛዥ ኮማንደር ደመላሽ ብርሃኑ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በወረዳው በሚገኙ 20 ቀበሌዎች ውስጥ በሚገኙ ሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁስ ያለምንም ፀጥታ ችግር ተሰራጭቷል።

ወረዳው ከመተከል ዞን ጋር ተዋሳኝ በሆኑ 34 ጣቢያዎች የሚከናወነው ምርጫ ያለ ጸጥታ ስጋት እንዲከናወን የተጠናከረ የፀጥታ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ጸጥታውን ለማስጠበቅ የክልሉ ልዩ ኃይል፣ መደበኛ ፖሊስና ፌዴራል ፖሊስ ተቀናጅተው እየሰሩ እንደሆነ አመልክተዋል።

ከሰሞኑም በአካባቢው ምርጫውን ለማደናቀፍ መከራ መደረጉን ገልጸው፤ ሙከራውን ያደረጉ ሃይሎች ዓላማቸው መክሸፉን ጠቅሰዋል።

ፖሊስ ከመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ጋር በመቀናጀት ምርጫውን በስኬት ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑንም ኮማንደር ደመላሽ አረጋግጠዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም