በአዲስ አበባ ሁሉም የትራንስፖርት አማራጮች ለምርጫው ከማለዳ ጀምሮ አገልግሎት ይሰጣሉ- ትራንስፖርት ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ሁሉም የትራንስፖርት አማራጮች ለምርጫው ከማለዳ ጀምሮ አገልግሎት ይሰጣሉ- ትራንስፖርት ቢሮ
አዲስ አበባ ሰኔ 13/2013 (ኢዜአ) ለነገው ምርጫ በአዲስ አበባ ሁሉም የትራንስፖርት አማራጮች ከማለዳ ጀምሮ አገልግሎት የሚሰጡ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ይርጋለም ብርሃኔ ለኢዜአ እንደገለጹት ለድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ በመዲናዋ የትራንስፖርት እጥረት እንዳይከሰት የዝግጅት ስራዎች ቀደም ብለው ተከናውነዋል።
በእለቱ የትራንስፖረት አገልገሎት አሰጣጡን የሚከታተል፣ የሚመራና ከየዘርፉ የተውጣጣ ግብረ ሃይል መቋቋሙንም ገልጸዋል።
የታክሲ አሽከርካሪዎችና ማህበራት፤ የብዙሃን ትራንስፖርት አቅራቢ ድርጅቶች ማለትም አንበሳ፣ ሸገርና ሃይገር ባሶች፣ የላዳ ሾፌሮችና ማህበራት ጋር ውይይት በማድረግ የስራ መመሪያ ማስቀመጥ መቻሉን አብራርተዋል።
ድጋፍ ሰጪ አውቶብሶችን በመጨመር አገልግሎቱ በተሳለጠ መልኩ እንዲሰጥ ይደረጋል ሲሉም አቶ ይርጋለም አረጋግጠዋል።
በዚህም በመዲናዋ ያሉ ሁሉም የትራንስፖርት አማራጮች ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የትራንስፖርት እጥረት ይከሰትባቸዋል የተባሉ አካባቢዎችን በመለየት ተጨማሪ ስምሪቶች የሚሰጡ መሆኑንም እንዲሁ።
በእለቱ የታክሲ አስተባባሪዎችና የትራንስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴዎች እጥረት ሲያጋጥም አፋጣኝ መፍትሄ የሚሰጡበት አሰራር ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።
የትራፊክ ፖሊሶች፣ የደምብ ልብስ የለበሱ የቢሮው ባለሙያዎችና የተቋቋመው ኮሚቴ በቅንጅት የሚሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአንበሳ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት በእለቱ 665 አውቶብሶችን ለትራንስፖርት ዝግጁ ማድረጉንም አረጋግጠዋል።
የድርጅቱ ዋና ስራአስኪያጅ አቶ ገበየሁ ዋቄ፤ በከተማዋ የትራንሰፖር አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት እንዲቻል የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
የድርጅቱ ሁሉም የአውቶብስ አሽከርካሪዎች፣ የቴክኒክ ባለሙያዎች፣ የድጋፍና የኦፕሬሽን ባለሙያዎች በነገው እለት በስራ ገበታቸው ላይ ተገኝተው አገልግሎት እንደሚሰጡም ተናግረዋል።
የምርጫ ካርድ የወሰዱ የድርጅቱ ሰራተኞችም ድምፅ በመስጠት በሽፍት ገብተው አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል ብለዋል።