ቀጥታ፡

ነዋሪዎቹ አገር ይመራል፣ ሕዝብ ያስተዳድራል ብለው ለሚያምኑበት ፓርቲ ድምጻቸውን ለመስጠት ተዘጋጅተዋል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 13 / 2013 (ኢዜአ) በምዕራብ ሸዋ ዞን የጉደር ከተማ ነዋሪዎች በነገው አገራዊ ምርጫ አገር ይመራል፤ ሕዝቡንም በአግባቡ ያስተዳድራል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምጻቸውን እንደሚሰጡ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ነገ ለሚካሄደው ምርጫ በጉደር ከተማ ኅብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ዝግጅት በመቃኘት ነዋሪዎችን አነጋግሯል፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ምርጫ የዴሞክራሲ መሰረት አንዱ መገለጫ በመሆኑ የሚፈልጉትን ፓርቲ ለመምረጥ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በምርጫው የሚሳተፉ የፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ መከታተላቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ፤ ይህም በድምፅ መስጫው ዕለት የሚሆናቸውን ለመምረጥ መረጃ ያገኙበት መሆኑን አክለዋል።

ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ቀደም ሲል ከተካሄዱ ምርጫዎች የተለየና ሠላማዊ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸውም ነው የተናገሩት፡፡

በወሰዱት የምርጫ ካርድ አገር ይመራል፣ ሕዝቡንም በአግባቡ ያስተዳድራል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምፃቸውን በነጻነት ለመስጠት መዘጋጀታቸውንም ነው የገለጹት፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለጻ ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ሁሉም አካል በሃላፊነት ሊንቀሳቀስ ይገባል።

ምርጫውን ተከትሎ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብን ድምጽ በጸጋ መቀበል እንዳለባቸውም ነው ያመለከቱት። 

ካርድ የወሰዱ ዜጎች በተለይም ወጣቶች ድምጻቸውን ለሚመርጡት ፓርቲ እንዲሰጡና የአካባቢያቸውንም ሠላም እንዲጠብቁ አስተያየት ሰጪዎቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ትውልዱ ወደፊት የሚሻውን ነገር ለማስፈጸም መራጩ ሕዝብ መሪውን በመምረጥ ተሳትፎውን እንዲያጠናከር ጠይቀዋል።

የኢዜአ ሪፖርተር ጉደር ላይ ባደረገው ቅኝት ከተማዋ በሠላማዊ እንቅስቀሴ ላይ መሆኗን ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም