ቀጥታ፡

ኢሰመኮ በምርጫው እለት የሰብአዊ መብቶች ክትትል ለማድረግ ባለሙያዎች ማሰማራቱን አስታወቀ

ሰኔ 13/ 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በማቋቋሚያ አዋጁ አንቀፅ 6 መሰረት በምርጫው እለት የሰብአዊ መብቶች ክትትል ለማድረግ ባለሙያዎች ማሰማራቱን አስታወቀ።

ነገ በሚካሄደው 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሰብአዊ መብቶችን ሁኔታ ለመከታተል ቡድኖች በማቋቋም ምርጫ በሚካሄድባቸው በሁሉም ክልሎች ባለሙያዎችን መሰማራቱን ገልጿል፡፡

ቡድኖቹ በሚሰማሩባቸው ስፍራዎች በምርጫው እለት እና ከምርጫው በኋላ ባሉት ቀናት በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ምልከታ የሚያደርጉ ሲሆን መራጮችን፣ የምርጫ አስተባባሪዎችን፣ የፀጥታ አካላትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ እጩዎችን፣ ታዛቢዎችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማነጋገር መረጃዎችን እንደሚያሰባስቡ አስረድቷል፡፡

እንደ ኢሰመኮ ገለጻ፤ ቡድኖቹ በፖሊስ ጣቢያዎች እና በሕክምና ተቋማት በመገኘት አስፈላጊውን ክትትል ያደረግሉ፡፡

ማንኛውም ሰው እና ተቋም በሙሉ የኢሰመኮ መለያ ካርድ (ባጅ) በመያዝ ለሚሰማሩት የኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ምርጫ ክትትል ቡድን አባላት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጠይቋል።

እንዲሁም ማንኛውም ሰው ለክትትል ቡድኖቹ አባላት ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ መረጃ እና ጥቆማ ማቅረብ የሚችል መሆኑን ገልጾ ከዚህም በተጨማሪ በኮሚሽኑ የነፃ የስልክ መስመር 7307 ላይ በመደወል መረጃ መስጠት እንደሚችል ኮሚሽኑ አሳውቋል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በምርጫው ወቅት ሰብአዊ መብቶች መከበራቸውን ማረጋገጥ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሀላፊነት መሆኑን አስታውሰዋል።

ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለኮሚሽኑ ስራ መሳካት ትብብር የማድረግ ግዴታቸውን እንዲወጡ እና በክትትል ስራ ለሚሰማሩ ባለሙያዎች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም