በቻግኒ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን የፀጥታ መዋቅሩ ዝግጅቱን አጠናቆ ተሰማርቷል... የከተማው ሰላምና ፀጥታ ፅህፈት ቤት - ኢዜአ አማርኛ
በቻግኒ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን የፀጥታ መዋቅሩ ዝግጅቱን አጠናቆ ተሰማርቷል... የከተማው ሰላምና ፀጥታ ፅህፈት ቤት
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13/2013 (ኢዜአ) በቻግኒ ምርጫ ክልል የፀጥታ መዋቅሩ በቂ ዝግጅት አድርጎ መሰማራቱን የቻግኒ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ፅህፈት ቤት ገለጸ።
የቻግኒ ከተማ የሰላምና ደህንነት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ኢንስፔክተር ተሰማ አጋዥ፤ የምርጫው ሂደት ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወን የጸጥታ መዋቅሩ በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።
የምርጫ ቁሳቁሶች እጀባ ተደርጎላቸው ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ማጓጓዝን ጨምሮ አስፈላጊው የፀጥታ ስምሪት ስለመደረጉ አንስተዋል።
እንደ ሃላፊው ገለፃ ከአካባቢው የፖሊስ፣ የሚሊሻና ልዩ ኃይል የተቀናጀ የፀጥታ ስምሪት ስራውን ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር እያከናወነ ነው።
የምርጫ ሂደቱ በድምፅ አሰጣጥም ይሁን በድህረ ምርጫ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወን የተቀናጀ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ኢንስፔክተር ተሰማ ገልጸዋል።
የኢዜአ ሪፖርተር በቻግኒ የምርጫ ክልል የተለያዩ ጣቢያዎች ባደረገው ቅኝትም የድምፅ አሰጣጡን ለማከናወን የሚያስችሉ ዝግጅቶች መደረጋቸውን አረጋግጧል።
በቻግኒ የምርጫ ክልል 72 የምርጫ ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን ከ49 ሺህ በላይ ዜጎችም የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።