የተንቀሳቃሽ ስልክ ቴክኖሎጂ ጉዳዮቻችንን በቀላሉ እንድናከናውን ረድቶናል-ተጠቃሚዎች

87
አዲስ አበባ ግንቦት 7/2010 በኢትዮጵያ ካለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት ወዲህ እየተስፋፋ የመጣው የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያቸውን በቀላል መንገድ ለመከወን እያስቻላቸው መሆኑን ተጠቃሚዎች ገለጹ። በአሁኑ ወቅት በመላው አገሪቷ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚው ህዝብ ቁጥር 64 ሚሊዩን መድረሱን ኢትዮ-ቴሌኮም አስታውቋል። ከተጠቃሚዎቹ መካከል መምህርት አማረች መንገሻ በተለይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት ከዚህ በፊት ከኢትዮጵያ ውጭ የምትኖር ታላቅ እህታቸው ጋር በመደበኛ ስልክ ለመገናኘት ቢያንስ ከሁለት ሰዓት ላላነሰ ጊዜ ከቤታቸው ትንሽ ራቅ ብሎ በሚገኘው ወዳጃቸው ቤት ቁጭ ብለው መጠበቅ ግድ ይሆንባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። "አሁን ግን የቴሌኮም ቴክኖሎጂና መሰረተ ልማት እያደገ በመምጣቱ ምንም ሳላስብ ባለሁበት አካባቢ አስፈላጊውን መረጃ ለመቀበልና ለመስጠት ብሎም ዘመዶቼን ለማግኝ እድሉን አግኝቼያለሁ" ብለዋል። ሐምሳ አለቃ ኃይለማርያም ዳምጠውም ይህንን ሀሳብ ይጋራሉ፤ “ስልክ ባልተስፋፋበት ጊዜ የምንጠቀመው እንደ አጋጣሚ አንድ ጎረቤት ስልክ ካስገባ እዚያ እየተጠራን ነው የምንጠቀመው፤ ይህም የአገሪቱ እድገት ነው ያመጣው፤ ቴክኖሎጂው እየተስፋፋ በመሔዱ ነው” ብለዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ ባለፉት ዓመታት በአገር ደረጃ ሁሉም ባለው አቅም የተንቀሳቃሽና የመደበኛ ስልክ ተጠቃሚ እንዲሆን መደረጉ ሕብረተሰቡ ጊዜና ቦታ ሳይገድበው በቀላሉ እንዲገናኝ "እድሉን አመቻችቶልናል" ነው የሚሉት። ለረጅም አመታት በሹፌርነት ሙያ ላይ የተሰማሩት አቶ ዘውዱ በቀለ በበኩላቸው "በአሁን ወቅት በተለይ የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት እያደገ መምጣት ስራዬን በቀላሉ እንዳከናውን አድርጎኛል" ብለዋል። በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ሲንቀሳቀሱ ባሉበት ስፍራ ሆነው የተሽከርካሪ ብልሽትም ሆነ ሌሎች የግል ጉዳዩችን በተንቀሳቃሽ ስልክ በቀላሉ መፍታት እየቻሉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። የኢትዮ-ቴሌኮም የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አብዱራሒም አሕመድ በበኩላቸው በአገሪቷ የቴሌኮም ዘርፉ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል። መንግስት በተለይም ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ ዘርፉን ለማሳደግ እየሰራ ነው። በአሁኑ ወቅት የክልሎችን ሕገ-መንግስታዊ የመልማት መብት መሰረት በማድረግ የስልክ መሰረተ ልማቱ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲዳረስ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል። በዚህ መሰረትም 85 ነጥብ 5 በመቶ በላይ የአገሪቷ የቆዳ ሽፋን የሞባይል አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል መሰረተ ልማት ተዘርግቷል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም