ቀጥታ፡

''ፖለቲካና ሃይማኖት'' ላይ ያተኮረ መጽሀፍ ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12/2013  ፖለቲካና ሃይማኖት-በሀገር ግንባታ ሂደት ሊኖሩ የሚገባቸው እሴቶችና ተግዳሮቶች የተሰኘውና በአምባሳደር ደግፌ ቡላ የተዘጋጀው መጽሀፍ ተመረቀ።

በመጽሐፉ ምረቃ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሠ ጫፎ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር ቀንዓ ያደታ እና ሌሎች የፌዴራልና ክልል መንግስት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የመጽሐፉ አዘጋጅ አምባሳደር ደግፌ ቡላ እንዳሉት፤ የሚያነብ ትውልድ ራሱንና አካባቢውን የሚለውጥና ለስልጣኔም መሰረት የሚጥል ነው።

"የስልጣኔ አንዱ ማሳያ ደግሞ የሌሎችን ሃይማኖት፣ ማንነት ማክበር ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር ጽንፍ የያዙ የሃይማኖትና ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች እየተንጸባረቁ መሆኑን በማስታወስ፤ መጽሐፉ ይህን በማስታረቅ ሚዛናዊ ትውልድ ለመቅረፅ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሠ ጫፎ በበኩላቸው "በትምህርት፣ በንባብና በህይወት ልምድ ያገኙትን እውቀትና ተሞክሮ ለትውልዱ ማስተላለፍ ትልቅ ሐሴት ነው" ብለዋል።

ሌሎች በተለያዩ የሥራ ሃላፊነትና የሙያ መስክ የተሰማሩ ዜጎችም ያነበቡትን፣ በህይወት ዘመናቸው ያጋጠሟቸውን ተግዳሮትና ስኬቶች መጪው ትውልድ እንዲማርበት በመጽሀፍ መልክ የማስቀመጥ ልምድ ሊያዳብሩ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ፕሬዚዳንት ጌታቸው በለጠ፤ "ብዙ ደራስያን በማይደፍሩት ርዕሰ ጉዳይ ላይ መጽሐፉን በማዘጋጀታቸው ምስጋና ይገባቸዋል" ሲሉ ገልጸዋል።

በአንድ ሀገር የተረጋጋ ማህበረሰብ መኖሩን ከሚጠቁሙ ጉዳዮች መካከል ሶስት ነገሮች በጉልህ ሲታዩ ነው ሲሉም ያብራራሉ።

"አንደኛው ፍቅረኛሞች ካለምንም ስጋት ነጻ ሆነው ሲንቀሳቀሱ፣ ሁለተኛው እርጉዝ ሴቶች በርከት ብለው ሲታዩና ሶስተኛው ደራስያን በአገራቸው የፖለቲካና ሃይማኖት ጉዳዮች ላይ መጻፍ ሲችሉ ነው" ብለዋል።

አምባሳደር ደግፌም በፖለቲካና ሃይማኖት ጉዳዮች መጽሐፍ በማዘጋጀት የተረጋጋ ማህበረሰብ መኖሩን አመላክተውናል ብለዋል አቶ ጌታቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም