ቀጥታ፡

ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የምርጫ ካርድ የወሰዱ የተለያዩ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

ሰኔ 12/2013  ቻግኒ / ሱሉልታ/ ደሴ   (ኢዜአ)   የምርጫ ካርድ የወሰዱ የተለያዩ  ከተማ ነዋሪዎች እለተ ሰኞ ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገለጹ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት ዘንድሮ ፓርቲዎች በነፃነት ራሳቸውን ያስተዋወቁበትና የገለጹበት አጋጣሚ በመሆኑ የሚፈለጉትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል።

በቻግኒ ከተማ ጂጂ ሰፈር ነዋሪዎች መካከል ወጣት ሀብታሙ ጌታሁንና ወጣት አሰፋ መረቅ  እንደሚሉትም ተወዳዳሪዎች ባሉበት  "ይበጀናል በተለይም ለወጣቶች ያገለግለናል" ያሉትን ዕጩ ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል። 

አቶ ንጋቸው ብዙነህ እና ቄስ ጌትነት አያሌው፤ ለአገርና ለወገን የሚጠቅመውን ፓርቲ ለመምረጥ የሰኞን ንጋት በጉጉት እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል ሱሉልታ ከተማ አስተዳደር ነዋሪ አቶ አግደው አዋሎ፤ በምርጫው ዕለት ለአገር ሰላምና ልማት ይበጃል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የዘንደሮው ምርጫ ሂደት እስካሁን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን ገልጸው እስከ ፍፃሜው በዚሁ መልኩ ይቀጥላል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ጆቴ ሴፈራ፤  የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ወደ አዲስ ምእራፍ በተሸጋገረበት አጋጣሚ በዘንድሮው ምርጫ ለመምረጥ በመታደላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ፓስተር ዲሪባ ሙሉነህ እና አቶ ወጋሪ ሲርቢሳ፤ በምርጫው ለአገርም ለህዝብም ይበጃል የምንለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ብለዋል።

ምርጫው በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲከናወን የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያን ከገጠማት ውስብስብና ፈታኝ ችግር ሊታደግ የሚችል ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ በደሴ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ናቸው።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የደሴ ከተማ አስተዳደር  ማስተባበሪያ በበኩሉ፤ ለምርጫው  ቅደመ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል።

በደሴ የሆጤ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ያሬድ መለሰ ለስድስተኛው ጠቅላላ  ምርጫ መንግስትና ምርጫ ቦርድ ያረጉት ቅደመ ዝግጅትና ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት ችግር ሊታደግ የሚችል ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ  ብለዋል፡፡

አቶ ዝናቡ በቀለ በበኩላቸው፤ መብቴንና ነጻነቴን ተጠቅሜ ኢትዮጵያ እየደረሰባት ካለው  የውጭ   ተጽዕኖና የመከፋፈል ችግር የሚታደግ እንዲሁም  የኑሮ ውድነትን ማስተካከል የሚችል ፓርቲ ለመምረጥ ዕለቱን እየተጠባበቅኩ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን  ሉዓላዊነት ጠብቆ ባህልና እሴቶቻችንን ለትውልድ የሚያስተላልፍ መሪ ለመምረጥ የፓርቲዎችን  ፕሮግራም በመከታተል  ድምጽ ለመስጠት መዘጋጀቱን የተናገረው ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ  ወጣት ኻሊድ አማረ ነው፡፡

''ድምጽ የሰጠሁት ፓርቲ ባያሸንፍ እንኳ ህዝብ የመረጠውን ለመደገፍ ዝግጁ ነኝ'' ብሏል።

በደሴ ከተማ አስተዳደር ባሉ 104 የምርጫ ጣያዎች 82 ሺህ 117 ዜጎች ለምርጫው ተመዝግበው  ካርድ መውሰዳቸውን ከማስተባበሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም