ቀጥታ፡

የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን 6ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለመታዘብ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12 ቀን 2013 (ኢዜአ) 28 አባላት ያሉት የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን 6ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለመታዘብ የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቀ።

የቡድኑ አባላት ምርጫውን ለመታዘብ የሚያስችላቸውን የይለፍ ወረቀት ተቀብለዋል።

በዚሁ ወቅት የቡድኑ ኃላፊ አምባሳደር አብዱላሂ አውሌድ አሊ ሜሲ እንዳሉት፤ ተጠባባቂ ሀይሉ በቀጣናው አስተማማኝ ሰላም፣  መረጋጋትና ልማት ለማረጋገጥ ይሰራል።

በዚህም በተደረገለት ግብዣ መሰረት የምርጫ መታዘቢያ ስነ ምግባር መርህን በመከተል ለመታዘብ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

የሕግ አስከባሪ አካላት የምርጫው ሂደት የተጠበቀ እንዲሆን ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የጠየቁት ሃላፊው፤ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና እጩዎች አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱንና የሰዎችን ሰብዓዊ መብት ሊያከብሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

መራጮች የዜግነት ግዴታቸውንና ሕገ መንግስታዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በምርጫው ላይ መሳተፍ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

አምባሳደር አብዱላሂ የምርጫ ታዛቢ ቡድኑ አባላት የሕግ የበላይነትን በማክበር ስራቸውን ሊያከናውኑ እንደሚገባም አሳስበዋል።

"ኢትዮጵያ የቀጣናው የመረጋጋት ምንጭ ናት" ያሉት የታዛቢ ቡድኑ ምክትል ኃላፊ ሊና ሁዋዎ በበኩላቸው፤ የነቃ የምርጫ መታዘብ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

"ያየነውን ሁሉ ሪፖርት ለማድረግ ዝግጁ ነን'' ብለዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሀይል ታዛቢ ቡድን እ.አ.አ ከ2018 ጀምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ምርጫ ሲታዘብ መቆየቱም ተገልጿል።

ታዛቢ ቡድኑ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ አፋር፣ ሲዳማ፣ ደቡብ፣ ድሬዳዋ እና በአዲስ አበባ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የምርጫውን ሁኔታ የሚከታተል መሆኑንም ባወጣው መግለጫ ገልጿል።


ታዛቢዎቹ በቆይታቸው ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ዓለም አቀፍ መርሆዎችን ባከበረ መልኩ መካሄድ አለመካሄዱን እንዲሁም የምርጫውን ግልጽነትና ታማኝነት በመከታተል ምርጫውን የተመለከተ ሪፖርት በማግስቱ ማክሰኞ እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል።

ከዚህ ቡድን በተጨማሪ በቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ሀላፊ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የተመራ የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ከትናንት በስቲያ ማምሻውን አዲስ አበባ መግባቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮውን ምርጫ ለሚታዘቡ 45 ሺህ የአገር ውስጥ ታዛቢዎች ፍቃድ ሰጥቷል።

ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ምርጫውን የሚታዘቡት በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ግብዣ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለታዛቢዎች የመታዘብ ፈቃድ ይሰጣል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም