በተለያዩ አካባቢዎች የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶች እየተከፋፈለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በተለያዩ አካባቢዎች የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶች እየተከፋፈለ ነው
ጎባ / መተማ / በተለያዩ አካባቢዎች የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶች እየተከፋፈለ ነው ።
ጎባ፣ግምቢ ሰኔ 12/2013(ኢዜአ) በባሌና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች ለስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶች ለየምርጫ ጣቢያዎች እየተከፋፈለ መሆኑን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዞኖቹ ጽህፈት ቤቶች ገለጹ፡፡
በቦርዱ የባሌ ዞን ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ፍርዲሳ ጋሮምሳ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ቁሳቁሶቹ እየተከፋፈሉ ያሉት በዞኑ በሚገኙ አምስት የምርጫ ክልል ውስጥ ለሚገኙ 552 የምርጫ ጣቢያዎች ነው።
ትናንት የተጀመረው የምርጫ ቁሳቁሶች ስርጭት እሩቅ በሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ጨምር እንዲደርሳቸው እየተደረገ መሆኑን አቶ ፍርዲሳ አስረድተዋል፡፡
የምርጫ ቁሳቁሶች በየጣቢያዎቹ እስኪደርሱና ከደረሱ በኋላም አስፈላጊው ደህንነትና ጥበቃ እንዲደረግላቸው ከፀጥታ አካላት ጋር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዞኑ ከ1ሺህ 600 ለሚበልጡ ምርጫ አስፈፃሚዎችም በመራጮች አመዘጋገብና በሰነድ አሞላል ላይ ስልጠና መሰጠቱንም ጠቅሰዋል፡፡
ህብረተሰቡ በመራጮች ምዝገባ ላይ ያሳየውን ተነሳሽነት በድምፅ መስጫ ቀን ላይ በመደገም የመብቱ ተጠቃሚ እንዲሆን አስተባባሪው ጥሪ አቀርበዋል።
በባሌ ዞን ሰኞ ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ከ500 ሺህ የሚበልጡ መራጮች ተመዝግበው የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውም ተመልክቷል፡፡
በተመሳሳይ በምዕራብ ወለጋ ዞን ለምርጫው የሚያስፈለጉ ቁሳቁሶች በዞኑ በሚገኙ ምርጫ ክልሎች ስር ላሉ የምርጫ ጣቢያዎች እየተከፋፈለ መሆኑን በቦርዱ የዞኑ ጽህፈት ቤት ገልጿል።
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ንጉሴ ታሪኩ እንዳሉት በዞኑ በሚገኙ ዘጠኝ የምርጫ ክልሎች ስር 664 የምርጫ ጣቢያዎች ምርጫ ይካሄዳል፡፡
ምርጫው ኮሮናን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎች በጠበቀ መልኩ በዞኑ 21 ወረዳዎች እና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ምርጫው እንደሚካሄድ አቶ ንጉሴ አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ በምዕራብ ጎንደር ዞኖች በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ መስጫ ቁሳቁሶች ደርሰዋል።
መተማ /ደብረ ማርቆስ -ሰኔ 12 /20 13 ( ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን በሁሉም ወረዳዎች በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ መስጫ ቁሳቁሶች መድረሳቸውን የዞኑ ምርጫ ቦርድ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በተመሳሳይ በምስራቅ ጎጃም ዞን በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ መስጫ ቁሳቁሶች እየተሰራጩ መሆኑን በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የዞኑ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገልጿል።
በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የምዕራብ ጎንደር ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ ወይዘሪት ተዋበች ግዛቸው ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ ለ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለድምጽ መስጫ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ዛሬ በሁሉም የምርጫ ክልሎች ደርሰዋል።
በዞኑ ሁለት ምርጫ ክልሎች ስር በተቋቋሙ 170 ምርጫ ጣቢያዎች ቁሳቁሶቹ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
የአምስት የምርጫ ጣቢያዎች ቁሳቁስ በመጓጓዝ ላይ እንዳለ በምርጫ ወቅት ለኮሮና መከላከያ አብሮ የተጫነ ሳኒታይዘር በመደፋቱ በድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ብልሽት ማጋጠሙን ተናግረዋል ።
በተበላሹ ወረቀቶች ምትክ እንዲላክ ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ መቅረቡን ተናግረዋል።
ከቦርዱ በምትክነት የተላከ የድምጽ መስጫ ወረቀት ጎንደር ከተማ ደርሶ ወደ ዞኑ እየተጓጓዘ መሆኑን ጠቁመው እንደደረሰ ዛሬውኑ ለምርጫ ጣቢያዎቹ እንደሚሰራጭ አመላክተዋል ።
የዞኑ ፖሊስና የህዝብ ሰላምና ደህንነት መምሪያዎች ቁሳቁሶች በየምርጫ ጣቢያዎች እንዲደርሱ ላደረጉት አስተዋጾ ምስጋና አቅርበዋል።
በተመሳሳይ በምስራቅ ጎጃም ዞን ለ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚያገለግል የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጨ መሆኑን በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የዞኑ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታውቋል ።
የጽህፈት ቤቱ አስተባባሪ አቶ ስለሺ ወርቅነህ ለኢዜአ እንደገለጹት ከቦርዱ የተላከ የድምጽ መስጫ ቁሳቁስ በዞኑ በስምንት ምርጫ ክልሎች ስር በተቋቋሙ 1ሺህ 451 ምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጨ ነው።
ምርጫ ጣቢያዎችን ለመራጮች ምቹ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።