በድምጽ መስጫው ዕለት ለሚያጋጥሙ ድንገተኛ የጤና ችግሮች ዝግጅት ተደርጓል...የቀይ መስቀል ማኅበር - ኢዜአ አማርኛ
በድምጽ መስጫው ዕለት ለሚያጋጥሙ ድንገተኛ የጤና ችግሮች ዝግጅት ተደርጓል...የቀይ መስቀል ማኅበር
ጎንደር፣ ሰኔ 12/ 2013(ኢዜአ) በጎንደር ከተማና ሦስት ዞኖች በድምጽ መስጫ እለት ሊያጋጥሙ ለሚችሉ ድንገተኛ የጤና ችግሮች የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ 106 የሰለጠኑ የቀይ መስቀል በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችንና 15 አምቡላንሶችን ማዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማህበር አስታወቀ።
በማህበሩ የጎንደርና አካባቢው ቅርንጫፍ ሃላፊ አቶ አታለል ታረቀኝ ለኢዜአ እንደገለጹት ቅርንጫፉ ጎንደር ከተማን ጨምሮ በማእከላዊ፣ በሰሜንና ምእራብ ጎንደር ዞኖች በድምጽ አሰጣጡ ሒደት ሊያጋጥሙ ለሚችሉ የጤና እክሎች ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል።
ማህበሩ ያሰማራቸው በጎ ፈቃደኞች ከማህበሩ አርማ ውጭ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ዓላማና ተግባር ጋር የማይወግኑ መሆናቸውን ገልጸው ለዚህም የመጀመሪያ ድረጃ ህክምና መስጫ ኪቶችን ጨምሮ ድንገተኛ ታማሚዎችን ወደ አንቡላንስ ማድረሻ ስትሬቸሮች መዘጋጀታቸውንም አስረድተዋል፡፡
ለምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች፤ በእድሜ ለገፉና ተጓዳኝ የጤና ችግር ላለባቸው ድምጽ ሰጪዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲሁም የእጅ ንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር እንደሚቀርብም ሃላፊው ተናግረዋል፡፡
ማኅበሩ በድምጽ መስጫው እለት የሚሰጠውን ሰብአዊ አገልግሎት ከሦስቱ ዞኖች ጤና መምሪያዎችና ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚያስችለውን የጋራ ስምምነት ማድረጉንም ሃላፊው አስታውቀዋል።
በጎንደር ከተማ የፊታችን ሰኞ በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ አሰጣጥ ስነ-ስርአቱን ሙሉ ቀን ለማከናወን በቂ ዝግጅት መደረጉን ከከተማው ምርጫ ክልል አስተባባሪዎች የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡