በሲዳማ ምርጫው ያለ ምንም የፀጥታ ስጋት እንዲከናወን ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ምርጫው ያለ ምንም የፀጥታ ስጋት እንዲከናወን ዝግጅት ተደርጓል
ሀዋሳ፣ ሰኔ 12/2013 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ያለምንም የፀጥታ ስጋት እንዲከናወን ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት ምርጫው ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከምንጊዜውም በላይ በገለልተኝነት ለማስፈፀም አቋም ተይዟል።
"አቋሙን እውን ለማድረግ ለረዥም ጊዜ ዝግጅት ስናደርግ ቆይተናል" ያሉት ኃላፊው በተለይ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ የፀጥታ ኮማንድ ፖስት ተደራጅቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ለመበታተን ጊዜው አሁን ነው ብለው የሚቋምጡ የውስጥና የውጭ ኃይሎች እንዳሉ ያነሱት አቶ አለማየሁ "ምኞቱ የመንግሥትን አቅምና ዝግጅት በአግባቡ ካለመረዳት የመነጨ አስተሳሰብ ነው" ብለዋል።
ምርጫው ሠላማዊ እንዳይሆን የሚንቀሳቀሱና እንደ ሀገር በሽብርተኝነት የተፈረጁ የህወሐትና ሸኔ የጥፋት ኃይሎችን ታሳቢ ያደረገ የፀጥታ ማስከበር ዝግጅት ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን አስታውቀዋል።
በክልሉ ምርጫው ሠላማዊ፣ ፍትሀዊ፣ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ እንዲካሄድ መደበኛ የፖሊስ አባላት ከምን ጊዜውም በላይ የገለልተኝነት ሚናቸውን እንዲወጡ ግንዛቤ ተፈጥሮ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
በሲዳማ ክልል የፀጥታ ስጋት እንደሌለ ያነሱት ኃላፊው ህብረተሰቡ ለሀሰተኛ መረጃዎች ጆሮ ከመስጠት ተቆጥቦ በምርጫው የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።
ምርጫውን ተገን በማድረግ የክልሉን ሠላም ለማወክ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ተላላኪዎች ስለማይጠፉ ህብረተሰቡ ለፀጥታ ኃይሉ ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።
ሰኔ 14 ቀን 2013 ድምፅ በሚሰጥባቸው ምርጫ ጣቢያዎች በቂ የፀጥታ ኃይል ተመድቦ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ሀላፊው አስታውቀዋል።