ቀጥታ፡

በምርጫው ሂደት የፀጥታና የደህንነት መዋቅሩ በኃላፊነትና ተጠያቂነት ግዴታውን ለመወጣት መዘጋጀቱን ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12/2013 ( ኢዜአ) በምርጫው ሂደት የፀጥታና የደህንነት መዋቅሩ በኃላፊነትና ተጠያቂነት ግዴታውን ለመወጣት መዘጋጀቱን ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ምርጫው ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲካሄድ አስፈላጊው ሁሉ ዝግጅት መደረጉን አስታውቋል።

ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ወሳኝ ምዕራፍ ከግምት ውስጥ በማስገባት የምርጫ ሂደቶች ከሁከትና ብጥብጥ የፀዱ ከጸጥታና የደህንነት መዋቅሩ ጋር የተቀናጀ የምርጫ ደህንነት እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን አስታውሷል። 

በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ዕለትና በድህረ- ምርጫ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ውስጣዊና ውጫዊ የፀጥታ ሁኔታዎችን በአግባቡ በመተንተን እና በመለየት አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ሲሰራ መቆየቱንም ገልጿል።

በመሆኑም ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ የፀጥታና የደህንነት መዋቅሮች በኃላፊነትና ተጠያቂነት የተሰጣቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት መወጣት የሚያስችላቸው ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ሥራ መግባታቸውን ይፋ አድርጓል።

የውስጥና የውጭ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ፀጥታውን ለማናጋት፣ የምርጫውን ሰላማዊነት ለማደፍረስና የሁከትና ብጥብጥ መንስኤ ለማድረግ እንደሚንቀሳቀሱ ከወዲሁ በመረዳት ምንም አይነት ህገ-ወጥ እንቅቃሴ በየትኛውም አካባቢ እንዳይኖር ዝግጅት መደረጉንም አረጋግጧል።

ለህዝቡ እና ለስራችን ከፍተኛ እገዛ የሚያደርጉት አስፈላጊና ወሳኝ የሆኑት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች በምርጫ ወቅት ያለበቂ ምክንያት እንዳይቋረጡ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም ኮሚሽኑ ጠይቋል።

የፀጥታ ሃይሉም መስዋትነት በመክፈል ጭምር ፍፁም ገለልተኛ ሆኖ ሌት ተቀን እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦ ምስጋናውን አቅርቦ በቀጣይ ለሚኖረው የድምጽ አሰጣጥና አጠቃላይ የምርጫ ሂደት ስኬታማነት ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነታችሁን እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ በብቃት እንድትወጡ ሲል አሳስቧል።

የምርጫ ህጉንና የስነ-ምግባር ደንብን አክብራችሁ እስካሁን ለምርጫ ሰላማዊነት የበኩላችሁን ገንቢ አስተዋጽኦ በማበርከታችሁ የኮሚሽኑ ምስጋና ላቅ ያለ ነው ብሏል።

በቀጣይም በሚኖረው የምርጫ ሂደት እስከ መጨረሻው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሀገራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ ሲል አሳስቧል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እና የጸጥታ ኃይሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ በመቀናጀት ይህንን ታሪካዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንድንወጣ ሲል ጥሪውን አቅርቧል።

በድምጽ መስጫ እለትና በድህረ- ምርጫ ወቅት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በህግ አግባብ ብቻ እንዲሆኑ ነው ያሳሰበው።

ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ለማጠናቀቅ ለሀገራችን ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ታላቅነት ለመላው ዓለም የምናሳይበት ታላቅ ኩነት ነው ያለው ኮሚሽኑ የምርጫው ሂደት አሁን ያለበት ደረጃ እስኪደርስ በጨዋነትና በትዕግስት ህዝቡ ላደረገው ድጋፍና ትብብር የላቀ ምስጋናውን አቅርቧል።

በቀጣይም ምርጫውን ለማደናቀፍ የሚያስችል አጠራጣሪ ጉዳይ ሲያጋጥም እንደተለመደው ሁሉ ህዝቡ መረጃ በመስጠትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለፀጥታ እና ለደህንነት ኃይሉ በማድረስ ትብብሩን እንዲያጠናክር ኮሚሽኑ ጠይቋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም