'ትስስር ለሕዳሴ ግድብ' ጥምረት ተመሰረተ - ኢዜአ አማርኛ
'ትስስር ለሕዳሴ ግድብ' ጥምረት ተመሰረተ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12 ቀን 2013 (ኢዜአ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በቅንጅት የሚሰራ "ትስስር ለሕዳሴ ግድብ" የተሰኘ ጥምረት በይፋ ተመሰረተ።
የጥምረቱ ምስረታ ላይ የተገኙት የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ አገራዊ ለውጡን ያልተቀበሉ አካላት ግድብ ተጠናቆ ወደ አገልግሎት እንዳይገባ በስውርና በግላጭ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
"ይሁን እንጂ ግድቡ አንድነታችንን እያጠናከረና ሉዓላዊነታችንን እያጎላና ኢኮኖሚው ከጥገኝነት እንዲላቀቅ መሰረት እየጣለ ነው" ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ ግንዛቤን ለማሳደግ በተበታተነ መልኩ የሚሰሩ ሥራዎችን ማቀናጀት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ለዚህም "ትስስር ለሕዳሴ ግድብ" የሚል ጥምረት ተመስርቶ ይፋ መደረጉን ተናግረዋል።
ጥምረቱ ስለ ዓባይ ግድብ ያለውን እውነታ ለዓለም ማህበረሰብ ለማስረዳት የሚሰራ ሲሆን በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ ምሁራንና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚናቸውን የሚወጡበት ነው።
የሙያ ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማትና የፖለቲካ ፓርቲዎች አባሎቻቸውንና ተከታዮቻቸውን በማስተባበር ለሕዳሴ ግድቡ ድምጽ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉበት እንደሆነም አክለዋል።
ኢትዮጵያዊያንን በአንድ አጀንዳ የሚያሰባስበው ጥምረቱ ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተጽዕኖ እንዲፈጥሩ የሚያስችላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
"አባቶች መስዋዕትነት ከፍለው አገሪቷን አስረክበውናል" ያሉት ዶክተር አረጋዊ፤ "እኛም ለቀጣዩ ትውልድ ግድቡን አጠናቀን በማስተላለፍ ታሪክ ማኖር አለብን" ብለዋል።
ጥምረቱ 12 አባላት ያሉት አስተባባሪ ኮሚቴ ያለው ሲሆን ሃብት አሰባሰብ፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ህዝባዊ ዲፕሎማሲ እንዲሁም መገናኛ ብዙሃንና ተግባቦትን ያካተተ ነው ተብሏል።
ከጥምረቱ አባላት መካከል የጊዜ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ መስራች ጊዜሽወርቅ ተሰማ ባለፉት ስምንት ዓመታት ስለግድቡ ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሲሞግቱ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
"ግድቡ በአሁኑ ወቅት እየተጠናቀቀና ወሳኝ ምዕራፍ ላይ በመድረሱ በተለይ ወጣቱ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ኢትዮጵያን ማገዝ አለበት፤ ልክ እንደሠራዊቱ በበይነ መረብ የአገሬን ሉአላዊነት አላስነካም ማለት አለበት" ሲሉም አክለዋል።