የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለልተኛነቱን የሚያረጋግጥ የሪፎርም ተግባር አከናውኗል - ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለልተኛነቱን የሚያረጋግጥ የሪፎርም ተግባር አከናውኗል - ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12 ቀን 2013 (ኢዜአ) “የአዲስ አበባ ፖሊስ በአስተሳሰብ የለውጥ ማዕከል የተቋሙን አቅም በማሳደግ ላይ ተመስርቶ ገለልተኛነቱን የሚያረጋግጥ የሪፎርም ተግባር አከናውኗል” ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አዲስ ፖሊሳዊ የደንብ ልብስ እና ዓርማ የማብሰሪያ መርሀ-ግብር ዛሬ በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል።
በማብሰሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትሯ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከስርአት አገልጋይነት የህዝብና የአገር አገልጋይ እንዲሆን በሚያስችል መልኩ እየተደራጀ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ሶስት አመታት የፖሊስ ተቋም ለውጥ ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስም በአስተሳሰብ የለውጥ ማዕከል የተቋሙን አቅም በማሳደግ ላይ መሰረት ያደረገ ገለልተኛነቱን የሚያረጋግጥ ተግባር እንዳከናወነ አብራርተዋል፡፡
ይህን በሚያረጋግጥ መልኩ የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከፌደራል መከላከያ ኃይል፣ ከሌሎች የጸጥታና ከፍትህ አካላት ጋር በመሆን በፈታኝ ወቅት ጭምር ስርአትን ሳይሆን ህዝቡንና አገርን ያስቀደመ ተግባር ማከናወን መቻሉን አንስተዋል፡፡
ለውጡ ፖሊስ ተፈርቶ ሳይሆን በህዝብ ዘንድ ተወዶ የሚከበር እንዲሆን ያስቻለ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ የአዲስ አበባን የፖሊስ ተቋም በዘመናዊ የሰው ሃይል፣ አስተሳሰብ፣ ስልጠናና በቴክኖሎጂ የማደራጀት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
“ይህም ተልዕኮውን በላቀ ብቃት እንዲወጣ ያስችለዋል” ብለዋል፡፡
በአሁኑ ሰአትም ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር ተቀራርቦ የመስራት ባህሉን እያደገ እንሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡