ቀጥታ፡

የቻይና ቀይ መስቀል ማህበር ለኢትዮጵያ 100 ሺህ ዶዝ የኮቪድ-19 ክትባት ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12/2013 ( ኢዜአ) የቻይና ቀይ መስቀል ማህበር ለኢትዮጵያ 100 ሺህ ዶዝ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባት ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን ዛሬ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አስረክቧል።  

ከተደረገው ድጋፍ 40 ሺህ ዶዝ ወደ ትግራይ ክልል የሚላክ መሆኑ ታውቋል።

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን፤ አገራቸው ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት መደገፏን ትቀጥላለች ብለዋል።

አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን በዚህ ወቅት "ኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሺኝን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ቻይና ትደግፋለች" ብለዋል።  

ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ድጋፍ ቻይና ማድረጓን ገልጸው ክትባቱ በርካታ ሰዎች ከወረርሺኙ  እራሳቸውን እንዲከላከሉ ይረዳቸዋል ብለዋል።

ቻይና በቀጣይም የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ በመቀጠል ኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚ እንድትገነባ የአጋርነት ሚናዋን እንደምትወጣ ገልጸዋል።

የጤና ሚንስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ፤ ቻይና ላደረገችው ድጋፍ አመስግነው ክትባቱ ወረረሺኙን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል።

ቻይና ከትባትም ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የመከላከያ ቁሳቁሶችንም ድጋፍ ማድረጓን አስታውሰው አሁንም የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

ቻይና የዛሬውን ጨምሮ ለኢትዮጵያ 500 ሺህ ዶዝ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባቶችን ድጋፍ አድርጋለች።

በኢትዮጵያ እስካሁን ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የኮቪድ 19 ክትባት መውሰዳቸውን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ ቀጥሎ በአፍሪካ ብዛት ያላቸው ዜጎችን በመከተብ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም