ቀጥታ፡

ስድስተኛውን የኢትዮጵያ ምርጫ ለመዘገብ ከ29 የውጭ ሚዲያዎች 89 ባለሙያዎች ገብተዋል

 ሰኔ 11/2013 (ኢዜአ) ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለመዘገብ ከ29 የውጭ መገናኛ ብዙሃን 89 ባለሙያዎች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አስታወቀ።

ፈቃድ አግኝተው ወደ አገር ውስጥ ከገቡት የመገናኛ ብዙሃን መካከል ቢቢሲ፣ አልጀዚራ፣ ሮይተርስ፣ ኒዮርክ ታይምስ፣ ኤፒ፣ ኤ.ኤፍ.ፒ፣ ዶቼ ቬሌ እና ቪ.ኦ.ኤ ተጠቃሽ ናቸው።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ እድሪስ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለሙያዎቹ አገር አቀፉን ምርጫ ለመዘገብ ፈቃድ ያገኙ ናቸው።

እስከ ሰኔ 11 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ፈቃድ ካገኙ 29 የውጭ መገናኛ ብዙሃን የተውጣጡት ጋዜጠኞች እና የካሜራ ባለሙያዎች ተካተዋል።

ምርጫውን የትኛውም የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በተለያየ መልኩ እንዲታዘብ፤ በተለይም የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ጋዜጠኞች እንዲዘግቡት ፍላጎት እንዳለም ነው የገለጹት።

"ፈቃድ የተሰጣቸው መገናኛ ብዙሀንም ሆኑ ጋዜጠኞች ግብዣ ተደርጎላቸው ሳይሆን አገራዊ ምርጫውን በተለየ መልኩ ሲከታተሉ ቆይተው ምርጫውን በራሳቸው በመዘገብ ለዓለም ማህበረሰብ ማስተላለፍ ፍላጎት በማሳደራቸው ወደ አገር ውስጥ የገቡ ናቸው" ብለዋል።

"ይህ የሚያሳየው በአገሪቱ የተፈጠረውን ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ተከትሎ ያለምንም እንቅፋት አገሪቱ ለውጪ ጋዜጠኞች ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ ሳይቀመጥ ክፍት መሆኗን ነው" ሲሉም አክለዋል።

ይህ ደግሞ የሪፎርሙ አካል እንደሆነ ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያመለከቱት።

በተጨማሪም የመገናኛ ብዙሃኑ ሁነቱን እና የምርጫውን አሳታፊነት፣ ግልጽነትና ፍትሀዊነት ለመዘገብ ያላቸውን ፍላጎት ያመላክታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአይነቱ የምታካሂደውን ልዩ ምርጫ ለመዘገብ መገናኛ ብዙሀኑ ከፍተኛ ጉጉትና ፍላጎት ስላላቸው በጀትና ባለሙያ መድበው ወደ አገር ውስጥ እየገቡ መሆኑንም ገልጸዋል።

ባለሙያዎቹ በኢትዮጵያ ቆይታቸው የአገሪቱን በጎ ገጽታ ለማየትና ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ነው አቶ መሀመድ የተናገሩት።

እንደ እርሳቸው ገለፃ እነዚህ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ደህንነታቸው እንደሚጠበቅ አረጋግጠዋል።

ባለስልጣኑም ባለሙያዎቹ የሚገጥማቸው ችግር ካለ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

ምርጫው እስከሚካሄድ ድረስ ህጋዊ ሰነድ አሟልተው ለሚመጡ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ባለስልጣኑ አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ ያለውን ዝግጁነትም ገልፀዋል።

"የምርጫው ሂደት በግልጽነት ተዘግቦ ለዓለም ማህበረሰብ መተላለፉ ኢትዮጵያ በዴሞክራሲ ሂደት እየሄደችበት ያለውን ርቀት እንዲመሰክሩ እድል የሚሰጥ ነው" ብለዋል።

ለመገናኛ ብዙሀኑ የተሰጣቸው ፍቃድ በጊዜ እንጂ በቦታ የተገደበ ባለመሆኑ ከባለስልጣኑ ጋር እየተገናኙ በየትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሰው መስራት እንደሚችሉ አቶ መሀመድ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም