ቀጥታ፡

በአገሪቷ ምርጫ በሚካሄድባቸው አካባቢዎቸ 4 ሺህ የሚጠጉ ታዛቢዎች ይሰማራሉ - የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት

ሰኔ 11/2013 (ኢዜአ) በመጪው ሰኞ ለሚካሄደው 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ 4 ሺህ የሚጠጉ የምርጫ ታዛቢዎችን እንደሚያሰማራ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ ገለጸ።

ኅብረቱ በድምጽ መስጫው እለት በድምጽ አሰጣጥና ቆጠራ እንዲሁም ድምጽ ከተሰጠ በኋላ ያለውን የምርጫ ሂደት በተመለከተ የሚኖረውን ትዝብት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የኅብረቱ አባል አቶ ሳህለስላሴ አበበ ምርጫው በአገሪቱ ዴሞክራሲን ለማስፈን እንደሚያስችል በማመን በዜጎች ዘንድ ተዓማኒ እንዲሆን ታዛቢዎችን በማሰልጠን እንዲሰማሩ ተደርጓል ብለዋል።

የኅብረቱ የትዝብት መርሃ ግብር በሳይንሳዊ መንገድ በተመረጠ የመረጃ አሰባሰብ ላይ የተመሰረተ መሆኑንና  በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ተመሳሳይ መጠይቆች እንዳሉት ገልጸዋል።

በምርጫው እለት እንደ ምርጫ ጣቢያዎች ብዛት ተመጣጣኝ ዘዴ በመጠቀም እስከ ሁለት ሺህ ታዛቢዎች የሚሰማሩ ሲሆን ቀሪዎቹ በአካባቢያቸው የምርጫ ጣቢያ በተንቀሳቃሽና ቋሚ ታዛቢነት ይሰማራሉ ብለዋል።

የኅብረቱ የምርጫ ትዝብት አስተባባሪ አቶ ቢኒያም አባተም "ታዛቢዎች በቀን ቢያንስ አምስት ጊዜ አዲስ አበባ ለሚገኘው የኅብረቱ የመረጃ ማዕከል የጽሁፍ መልዕክት ይልካሉ" ብለዋል።

ድምጽ መስጠት ከመጀመሩ በፊት ያለውን ዝግጅት በተመለከተ፣ ድምጽ መስጠት ሲጀመር፣ ቀን የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱንና የድምጽ ቆጠራው ተጠናቆ ውጤት ከተለጠፈ በኋላ ሪፖርት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

የምርጫ ታዛቢዎች ነፃና ገለልተኛ እንዲሆኑ በማሰብ ሁሉም ከሲቪክ ማህበራት መመልመላቸውንና የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዳልሆኑ በቃለ መሀላ ጭምር ማረጋገጣቸው ተገልጿል።

ኅብረቱ ከ175 በላይ የሲቪክ ማኅበራትን ያቀፈና ምርጫው ፍትሃዊና ተዓማኒ ሆኖ በሠላም እንዲጠናቀቅ ችግሮች ከተከሰቱም አፋጣኝ መፍትሄ እንዲያገኙ ለማስቻል የተቋቋመ አገር በቀል ድርጅት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም