ምርጫው ያለምንም የጸጥታ ስጋት እንዲጠናቀቅ ከኅብረተሰቡ ጋር እየሰራን ነው - የአምቦ ከተማ ሠላምና ጸጥታ - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫው ያለምንም የጸጥታ ስጋት እንዲጠናቀቅ ከኅብረተሰቡ ጋር እየሰራን ነው - የአምቦ ከተማ ሠላምና ጸጥታ
ሰኔ /2013 (ኢዜአ) በመጪው ሰኞ የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ያለምንም የጸጥታ ስጋት እንዲጠናቀቅ ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የአምቦ ከተማ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ገለፀ፡፡
የአምቦ ከተማ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ባይሣ ሁሴን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በከተማዋ የቅድመ ምርጫ ሂደቶች በሠላማዊ ሁኔታ መካሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡
የምርጫው የድምፅ መስጫ ዕለትም ሠላማዊ እንዲሆን ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነወ ብለዋል።
ኅብረተሰቡ በድምጽ መስጫው ቀን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚፈልገውን እንዲመርጥም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአምቦ ከተማ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተደራጀ መልኩ የአካባቢያቸውን ሠላም በመጠበቅ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ምርጫውን ሰላማዊ ለማድረግም የአምቦ ከተማ የጸጥታ አካል በቂ ዝግጅት ማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡
የአምቦ ከተማ ወጣቶችም በብሎክ በተደራጁ የኮሚዩኒቲ ፖሊሲንግ አባል በመሆን ከጸጥታ ሃይሉ ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውን ነው አቶ ባይሳ የገለጹት፡፡
ወጣቱ እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
እንደ ፀጥታ ቢሮው ሃላፊ ገለጻ በከተማዋ የሚገኙ የፌዴራል ፖሊስና የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባላት እንዲሁም የአምቦ ከተማ መደበኛ ፖሊሶች የምርጫውን ሠላማዊነት ለማስጠበቅ በቅንጅት እየሠሩ ነው።
የስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን በመጪው ሰኞ ሰኔ 14 ቀን መሆኑ ይታወቃል፡፡