ቀጥታ፡

ወይዘሪት ሄራን ገርባ የዓለም ጤና ድርጅት የ2021 ሲጋራ የማይጨስበት ቀን ሽልማት አሸነፉ

ሰኔ /2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር  ሄራን ገርባ በትምባሆ ቁጥጥር ፕሮግራም ላሳዩት በሳል አመራር የዓለም ጤና ድርጅት የ2021 ሲጋራ የማይጨስበት ቀን ሽልማት አሸነፉ።

ዳይሬክተሯ የድርጅቱን ሽልማት ያገኙት በኢትዮጵያ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ሲጋራ እንዳይጨስ የወጣውን መመሪያ በማስተግበርና በመቆጣጠር ላደረጉት አስተዋጽ ነው ተብላል።

በእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የዓለም የጤና ድርጅት ተጠሪ ዶክተር ቡሬማ ሳምቦ በኢትዮጵያ ከሲጋራ ነጻ አካባቢ ለመፍጠር፣ በትምባሆ ምርቶች ላይ የተደረገ የታክሰ ጭማሪና የተወሰዱ እርምጃዎች የሚደነቁ ናቸው ብለዋል።

"ዳይሬክተሯ በትምባሆ ቁጥጥር ላይ በተሰጣቸው ኃላፊነት በትጋት በመስራታቸውና ላሳዩትም ለውጥ ሽልማቱ ይገባቸዋል" ብለዋል።

ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2014 ጀምሮ በትምባሆ ቁጥጥር ባሳየችው አፈጻጸም ለ5ተኛ ጊዜ ተሸላሚ መሆኗንም ተወካዩ ገልጸዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በትምባሆ ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር ለመደገፍ ቁርጠኛ እንደሆነ ገልጸው፣ በቁጥጥር ሥራው የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ሥራ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፤ በባለስልጣኑ በሳል አመራር በትምባሆ ቁጥጥር ላይ በተከታታይ የተገኙት ጉልህ ስኬቶች ለሽልማቱ ለመታጨት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ወይዘሪት ሄራን የትምባሆ ቁጥጥር ሥራው ስትራቴጂክ ፕላን እንዲኖረውና በሳይንሳዊ መረጃ ተመስርቶ  እንዲመራ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች፣ ድጋፍና አመራር ሲሰጡ እንደነበረም ገልጸዋል።

ለዚህም በትምባሆ ምርቶች ላይ በተለይ አገር ውስጥ በሚመረቱ የሲጋራ ምርቶች ፓኮዎች ላይ የጤና ማስጠንቀቂያ ምልክቶቹ 70 በመቶ እንዲሸፍን በማድረገ ትልቅ ሥራ መሰራቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የትምባሆ ኢንደስትሪውም በዚህ ረገድ ጣልቃ እንዳይገባ በርካታ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውንም ነው የጠቆሙት።

ዶክተር ሊያ በትምባሆ ቁጥጥር ሥራዎች ላይ ያለውን ክፍተት በመፈተሽና በማጠናከር ባለድርሻ አካላት እስካሁን ላደረጉት አስተዋፅኦም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ በትምባሆ ቁጥጥር ላይ የተሰራው ሥራ አበረታች ነው በሚል ሽልማቱ እንዲሰጥ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

ሽልማቱ የተገኘው የተቋሙ ሠራተኞችና ባለድርሻ አካላት ባደረጉት አስተዋጽኦ መሆኑን ገለጸው፤ "ሽልማቱ የጋራ ሥራና በጋራ የመጣ ውጤት ነው" ብለዋል።

በትምባሆ ቁጥጥር የአጫሾችን ቁጥር ከመቀነስ አኳያ አየተሰሩ ያሉ ሥራዎች በቂ እንዳልሆኑን ሽልማቱም ተጨማሪ ሥራዎችን ለመስራት ትልቅ ማነቃቂያ መሆኑን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

ለዚህም የመንግስትና የተጠሪ ተቋማት ቅንጅታዊ ሥራና የማህበረሰቡ ድጋፍ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

ሲጋራ የማይጤስበት ቀን በየዓመቱ ግንቦት 23 ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም