በዓመት ከ15 ሺህ ጊጋ ዋት በላይ ሀይል የሚያመነጨው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ 80 ነጥብ 2 በመቶ መድረሱ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በዓመት ከ15 ሺህ ጊጋ ዋት በላይ ሀይል የሚያመነጨው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ 80 ነጥብ 2 በመቶ መድረሱ ተገለጸ
አዲስ አበባ ሰኔ 11/2013 በዓመት ከ15 ሺህ ጊጋ ዋት በላይ ሀይል እንደሚያመነጭ የሚጠበቀው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም 80 ነጥብ 2 በመቶ መድረሱ ተገለጸ፤ ተያያዥ የግንባታ ሥራዎች እየተቀላጠፉ መሆኑም ተነግሯል።
የግድቡ ግንባታ አሁናዊ ሁኔታ ገለጻ፣ 'የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል' ምስረታና ሶፍትዌር ይፋ ማድረጊያ መርሃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች በበይነ መረብ ታድመዋል።
አቶ ደመቀ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ጨምሮ በምርጫ፣ በትግራይ የህግ ማስከበርና ተያያዥ ጉዳዮች ጫናዎችን እያስተናገደች ትገኛለች።
በተለይም ዲፕሎማሲያዊ ጫናው እየጠነከረ መምጣቱን ተከትሎ ይህን ለመመከት ብሔራዊ ትብብር የሚያስፈልግበት ወቅት መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።
"ለዚህ ሥራ መሳካት ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ምሁራንና ተማሪዎች ሚናቸው ትልቅ መሆኑን መረዳት አለባቸው" ብለዋል።
ኢትዮጵያ የያዘችውን የእውነት መንገድ ተንትኖ ማቅረብ የነገ ተስፋዋ በሆኑት ተማሪዎቿ ላይ የተጣለ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
"የክፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከልም በግድቡ ዙሪያ የሚነዙ ያልተገቡ መረጃዎችን ለመመከት ላቅ ያለ ጥቅም አለው" ብለዋል አቶ ደመቀ።
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለም የግድቡ ግንባታ ሂደት በተሻለ መልኩ እየተሳለጠ መሆኑን በገለጻቸው ጠቁመዋል።
15 ሺህ 692 ጊጋ ዋት ሀይል እንደሚያመነጭ የሚጠበቀው ታላቁ የኢትጵያ ሕዳሴ ግድብ በአሁኑ ወቅት ጠቅላላ ግንባታው 80 ነጥብ 2 በመቶ መድረሱንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም "የሲቪል ሥራው 91 ነጥብ 2 በመቶ፤ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራው 52 ነጥብ 7 በመቶ እንዲሁም የሀይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታው 100 በመቶ ተጠናቋል" ብለዋል።
በዚሁ መሰረት በመጪው ክረምት ውሃ የመያዝና በተያዘው ውኃ ደግሞ በሁለት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት እንደሚጀመር አረጋግጠዋል።
እስከ ቀጣዩ ዓመት ሰኔ ድረስ ደግሞ በአራት ተርባይኖች ሀይል ማመንጨት ለመጀመር ውጥን መኖሩን ነው ዶክተር ስለሺ ያስረዱት።
ግድቡ ሲጠናቀቅ ከፍተኛ የመስኖ ልማት ሥራ መስራት የሚያስችል፣ የዓሣ ሀብት ልማትና የቱሪዝም ዘርፍ ጥቅሞቹ አያሌ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
የሳይንስና ክፍትኛ ትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በበኩላቸው "ይፋ የተደረገው ሶፍትዌር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የሚያስተሳስር ነው" ብለዋል።
"ናይል ኔሽንስ" የሰተኘው ሶፍትዌር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ተማሪዎች በቀላሉ "የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል" ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ እንደሚያግዝ ገልፀዋል።
ይህም ዜጎች በትክክለኛ መረጃና በእውነት ላይ ተመርኩዘው ግድቡን በተመለከተ ክርክር ላይ እንዲሳተፉ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
የተመሰረተው ማዕከል ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር ያገኟቸውን ውጤቶች ለመለዋወጥ እድል ይሰጣል የሚል ተስፋ እንደሰነቁ የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ናቸው።
"በሃቅና በእውነት ላይ ያልተመሰረተ እንዲሁም በጥናትና ምርምር ያልታገዘ ዲፕሎማሲ ፍሬያማ አይሆንም" ያሉት ፕሮፌሰሩ ዩኒቨርሲቲዎች ምርምራቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
በገለጻ መርሃ ግብሩ ላይ ከ45 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተወከሉ ሁለት ሺህ ገደማ ሰዎች በበይነ መረብ መሳተፋቸው ተገልጿል።