የይድነቃቸው ተሰማ መታሰቢያ የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ውድድር ከነገ በስቲያ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የይድነቃቸው ተሰማ መታሰቢያ የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ውድድር ከነገ በስቲያ ይጀመራል
አዲስ አበባ ሀምሌ 28/2010 13ኛው የክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ መታሰቢያ የታዳጊ ወጣቶች ውድድር ሰኞ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ይጀምራል። ውድድሩን ያዘጋጀው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ነው። ውድድሩ ምንም አይነት የውድድር ዕድል ያላገኙ ዕድሜያቸው ከ14 እስከ 15 ዓመት በሆኑ ታዳጊ ቡድኖች መካከል የሚካሄድ ሲሆን በአጠቃላይ 88 ቡድኖች ይሳተፉበታል። በውድድሩ 80 የአዲስ አበባ ቡድኖች የሚሳተፉ ሲሆን የተቀሩት የክልል ቡድኖች ናቸው። የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ምንሊክ ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት "በየዓመቱ የሚካሄደው ውድድር ዋነኛ ዓላማው ተተኪ ተጫዋቾችን ማፍራት ነው።" በውድድሩ ለመሳተፍ 122 ቡድኖች ከአዲስ አበባና ከክልል ከተሞች የተመዘገቡ ቢሆንም በተደረገው የእድሜ ተገቢነት የማጣራት ስራ ትክክለኛውን የእድሜ ገደብ ያሟሉና ብቁ ሆነው የቀረቡት 88 ቡድኖች መመረጣቸውን አስረድተዋል። በውድድሩ መክፈቻ ዕለት በዶን ቦስኮ የካቶሊክ ትምህርት ቤት ውስጥ በሁለት ሜዳዎች ስምንት ጨዋታዎች እንደሚደረጉም ተናግረዋል። በቀደሙት ተመሳሳይ ውድድሮች ምንተስኖት አዳነ፣ ናትናኤል ዘለቀ፣ ኤልያስ ማሞ፣ አህመድ ረሺድ (ሽሪላ)ን የመሳሰሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች የተገኙ መሆኑንና ዘንድሮም በርካታ ተጫዋቾች ይታያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል። ውድድሩን እስከ ጳጉሜ ወር 2010 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እቅድ መያዙንም ጠቁመዋል። ይድነቃቸው ለአንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ለ23 ዓመታት ተጫውተው ያሳለፉ ሲሆን፤ በእነዚህ የ23 አመታት ቆይታ ይድነቃቸው በጊዜው ዝነኛ ተጫዋች ነበሩ። ይድነቃቸው የፈረንሳይ ፉትቦል ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንቦችን መሰረት በማድረግ የእግር ኳስ ህጎችን ወደ አማርኛ ተርጉመው የኢትዮጵያ እግር ኳስ በህግና ደንብ እንዲመራ መሰረት መጣል ችለዋል። በኢትዮጵያ ዘመናዊ ስፖርትን ያስፋፉና ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ያደረሱ በኳስ ተጫዋችነት በአሰልጣኝነት በእግር ኳስ አመራር ሰጪነት በመሳተፍ በስፖርቱ ዓለም ምኞታቸውን ማሳካት የቻሉ ታላቅ የስፖርት ሰው ናቸው። በሌላ የፕሪሚየር ሊግ ዜና የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ የጅማ አባጅፋር እግር ኳስ ክለብ አዲስ አሰልጣኝ እያፈላለገ መሆኑን አስታውቋል። የቡድኑ አሰልጣኝ የነበሩት ገብረመድህን ኃይሌ ከክለቡ መልቀቃቸውን ተከትሎ በዘንድሮው የውድድር ዓመት የመቀሌ ከተማ አሰልጣኝ የነበሩት ዮሐንስ ሳህሌ ክለቡን ለአንድ ዓመት ለማሰልጠን የውል ስምምነቱን በይፋ እንደሚፈርሙ ተገልጾ ነበር። ነገር ግን አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ውላቸውን በይፋ በሚፈርሙበት ሐምሌ 24 ቀን 2010 ዓ.ም በጅማ ከተማ አለመገኘታቸውን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ እስከዳር ዳምጠው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጸዋል። በአሁኑ ሰዓት ክለቡ አዲስ አሰልጣኝ ለመሾም ከተለያዩ አሰልጣኞች ጋር ድርድር እያደረገ መሆኑን ነው አቶ እስካዳር ያስረዱት። በድርድር ላይ ካሉት አሰልጣኞች መካከል የፋሲል ከተማ አሰልጣኝ የነበሩት ዘማርያም ወልደ ጊዮርጊስ የተሻለ እድል እንዳላቸውና ቀጣዩ የክለቡ አሰልጣኝ እንደሚሆኑ ፍንጭ ሰጥተዋል። ከጅማ አባጅፋር ጋር የኮንትራት ውል ያልተፈራረሙት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በአንድ ዓመት ውል ስምምነት ድሬዳዋ ከተማን ለማሰልጠን እንደተስማሙ ከክለቡ የህዝብ ግንኙነነት ክፍል የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ትናንት ከክለቡ ጋር የስምምነት ፊርማቸውን ያኖሩት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከዛሬ ጀምሮ ቡድናቸውን ማደራጀት እንደሚጀምሩ ክለቡ ገልጿል።