ቀጥታ፡

በጥሞና ወቅትም ሆነ በምርጫው ዕለት የምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉና መልዕክት በሚያስተላልፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል

አዲስ አበባ ሰኔ 11/2013 በጥሞና ወቅትም ሆነ በምርጫው ዕለት የምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉና መልዕክት በሚያስተላልፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በጥሞና ወቅትና በድምጽ መስጫ ዕለት ማድረግ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ከፖለቲካ ፖርቲዎች ጋር ውይይት እያደረገ ነው።

የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ እንዳተናገሩት፤ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በጥሞና ወቅትም ሆነ በድምጽ መስጫው ዕለት የምርጫ ቅስቀሳ ወይም መልዕክት ማስተላለፍ አይችልም።

ምርጫ ቦርድ ይሄንን ተላልፎ የተገኘ የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ እጩ ተወዳዳሪ ላይ አጣርቶ እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል።

ወይዘሪት ብርቱካን እንዳብራሩት፤ የምርጫ ቅስቀሳም ሆነ መልዕክት የሚያስተላልፍ የፖለቲካ ፓርቲ አለ በሚል በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመስርቶ የሚቀርብ ማንኛውም ቅሬታ ታይቶና ተጣርቶ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል።

ከዚህ በተጨማሪ የመገናኛ ብዙሀንም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ከቦርዱ በፊት ውጤት ይፋ ማድረግ እንደማይችሉም ተናግረዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ለትራንስፖርት አመቺ ባልሆኑ ወይም የጸጥታ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች በአየር ሀይል ተጠቅሞ የምርጫ ቁሳቁሱን ከምርጫው በፊት ለማድረስ ከአመራሩ ጋር በመስራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም