ስደተኞችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል የፕሮጀክት ስምምነት ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ስደተኞችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል የፕሮጀክት ስምምነት ተደረገ
አዲስ አበባ ሰኔ 11/2013 (ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት ዋይዝ ከተሰኘ የራስ አገዝ ሴቶች ድርጅት ጋር በከተሞቸ የሚገኙ ስደተኞችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል የፕሮጀክት ስምምነት አደረገ።
የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አና ኢንኮንትሬ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በከተሞች ለሚገኙ ስደተኞችና ስደተኞቹን ተቀብለው ለሚያስተናግዷቸው ማህበረሰቦች ዘላቂ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ነው።
የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ፕሮጀክቱ ለስደተኞችም ሆነ ለአካባቢው ነዋሪዎች ተጨባጭና ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሆን ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ከሚገኙ ስደተኞች 55 በመቶ የሚሆኑት ትምህርት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፣ "ይህም የወደፊት ተስፋቸው እንዲለመልም ያደርጋል" ብለዋል።
"ስደተኞቹ ትምህርት እንዲያገኙ የተደረገው በኢትዮጵያ መንግስት ጥረት በመሆኑ ትልቅ ምስጋና ይቸረዋል" ያሉት ተወካዩ፣ ድርጅቱም ስደተኞች በኢትዮጵያ ትምህርት እንዲካተቱና የተሻለ እድል እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ከቀያቸው ለቀው ለስደት መዳረጋቸውንና ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመትም ከ80 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በተለያዩ አገራት መሰደዳቸውን ጠቅሰዋል።
ይህ ቁጥር ከ10 ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ እንደሚበልጥና ስደተኞቹ ከአገራቸውና ከቀያቸው በጦርነት፣ በግጭትና በመሳሰሉት ምክንያቶች የተሰደዱ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የራስ አገዝ ሴቶች ድርጅት /ዋይዝ/ ዳይሬክተር ጽጌ ሃይሌ ድርጅቱ ከ23 ዓመታት በላይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉና ማህበራዊና ኢኖኮሚያዊ ችግሮች ያሉባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችና ሴቶች ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ ሲያግዝ መቆየቱን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር ስደተኞች ኑሯቸውን ለማሻሻል የሚያበቋቸውን የተለያዩ አገልግሎቶች እንዲያገኙ እየሰራ ነው ብለዋል።
በፕሮጀክቱ ለ3 ሺህ ሰዎች ተደራሽ እንደሚሆኑና 1 ሺህ 500 ያህሉ ኢትዮጵያዊያን ቀሪዎቹ ደግሞ ከተለያዩ አገራት በተለይ ከኤርትራና ከሶማሊያ የተፈናቀሉ ስደተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።
"በፕሮጀክቱ ስደተኞች በተለያየ የስልጠና መርሃ ግብር ታግዘው የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው እገዛ ይደረጋል" ነው ያሉት።
የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ፤ በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ዜጎች የምግብ፣ የጤናና የትምህርት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ900 ሺህ በላይ ስደተኞች እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ስደተኞቹ ከ26 አገራት የመጡ ሲሆኑ በዋናነት ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያ፣ ከኤርትራ እና ከሱዳን የመጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ስደተኞቹ በመላ አገሪቷ በሚገኙ 25 የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችና በዋና ዋና ከተሞች እንደሚገኙም አብራርተዋል።