ቀጥታ፡

ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ለብሔራዊ ቡድኑ 34 ተጫዋቾችን ጠርተዋል

አደዲስ አበባ ሀምሌ 28/2010 ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የተመረጡት ኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን አባላት ጥሪ ተደረገላቸው። በቅርቡ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ሆነው የተሾሙት አብርሃም መብራቱ ጥሪ ያደረጉት ከሴራሊዮን ጋር ጳጉሜ 4 ቀን 2010 ዓ.ም ላለባቸው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ለ2019 ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም ጀምሮ ዝግጅት ማድረግ እንደሚጀምሩም ተገልጿል። ከ20 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያና የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ለማድረግ መስማማታቸውን ተከትሎ በነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በአስመራ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ለኢንስትራክተር አብርሃም የመጀመሪያ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታቸው ሲሆን በ2019 በካሜሮን በሚካሄደው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ብሔራዊ ቡድኑ በመስከረም ወር 2011 ዓ.ም ከሴራሊዮን ጋር ለሚያደርገው የማጣሪያ ጨዋታም አቋም መፈተሻ የሚሆን ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ ጨዋታዎችን ያደረገው በኬንያ አስተናጋጅነት ከህዳር 24 እስከ ታህሳስ 8 ቀን 2010 ዓ.ም በተካሄደው የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) የእግር ኳስ ውድድር ላይ ነው። በውድድሩ ብሔራዊ ቡድኑ ደቡብ ሱዳንን ሶስት ለዜሮ አሸንፎ፣በብሩንዲ አራት ለአንድ በሆነ ሰፊ የጎል ልዩነት ተሸንፎና ከኡጋንዳ ጋር አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተለያይቶ አራት ነጥብ ሰብስቦ ከምድቡ ማለፍ ሳይችል መቅረቱ የሚታወስ ነው። በታህሳስ ወር 2010 ዓ.ም የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ የነበሩት አሸናፊ በቀለ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር መለያየታቸው ተከትሎ ለሰባት ወራት ቡድኑ አሰልጣኝ ሳይቀጠርለት ቆይቶ ነበር። ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ለሁለት አመት ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር እንዲቆይ ስምምነት መደረሱንም ይታወሳል ከሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ውጭም በወር የተጣራ 125 ሺህ ለአሰልጣኙ ይከፈላቸዋል። ሐምሌ 23 ቀን 2010 ዓ.ም አሰልጣኙ በይፋ ውል በተፈራረሙበት ወቅት እ.አ.አ በ2020 ኢትዮጵያ ለምታስተናግደው የአፍሪካ አገራት እግር ኳስ ውድድር (ቻን) ጠንካራ እና ተፎካካሪ ቡድንን መገንባት እና በ2019 በካሜሮን በሚካሄደው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ እቅዳቸው ነው። በኢንስራክተር አብርሃም መብራቱ ለብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት ጥሪ የተደረገላቸው 34 እጩ ተጫዋቾች ዝርዝር ከዚህ በታች እንደሚከተለው ቀርቧል። ግብ ጠባቂዎች አቤል ማሞ (መከላከያ) ሳምሶን አሰፋ (ድሬዳዋ ከተማ) ተክለማርያም ሻንቆ (ሀዋሳ ከተማ) ፂዮን መርዕድ (አርባምንጭ ከተማ) ተከላካዮች ሳልሀዲን ባርጌቾ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) አስቻለው ታመነ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ሙጂብ ቃሲም (ፋሲል ከነማ) አዲሱ ተስፋዬ (መከላከያ) ተመስገን ካስትሮ (ኢትዮጵያ ቡና) አንተነህ ተስፋዬ (ድሬዳዋ ከተማ) አብዱልከሪም መሀመድ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ኄኖክ አዱኛ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ዐወት ገብረሚካኤል (ኢትዮ ኤሌክትሪክ) አህመድ ረሺድ (ኢትዮጵያ ቡና) አምሳሉ ጥላሁን (ፋሲል ከተማ) ሰለሞን ሀብቴ (ፋሲል ከተማ) አማካዮች ጋቶች ፓኖም (ኤል ጉና ግብጽ) ሙሉአለም መስፍን (ቅዱስጊዮርጊስ) ናትናኤል ዘለቀ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) አማኑኤል ዮሀንስ (ኢትዮጵያ ቡና) ቢኒያም በላይ (ስኬንደርቡ ኮርሲ አልባኒያ) ከነዓን ማርክነህ (አዳማ ከተማ) ሽመልስ በቀለ (ፔትሮጀት ግብጽ) በዛብህ መለዮ (ፋሲል ከተማ) ታፈሰ ሰለሞን (ሃዋሳ ከተማ) አጥቂዎች አዲስ ግደይ (ሲዳማ ቡና) አቤል ያለው (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ዑመድ ኡኩሪ (ስሞሀ ግብጽ) በኃይሉ አሰፋ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ጌታነህ ከበደ (ደደቢት) አማኑኤል ገብረሚካኤል (መቐለ ከተማ) ዳዋ ሁቴሳ (አዳማ ከተማ) እስራኤል እሸቱ (ሃዋሳ ከተማ) አቡበከር ነስሩ  ከኢትዮጵያ ቡና ለብሄራዊ ቡድን የተመረጡ ተጫዋቾች ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም