በጋምቤላ ክልል ከ1ሺህ 119 ኪሎ ግራም በላይ የወርቅ ምርት ለብሔራዊ ባንክ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል ከ1ሺህ 119 ኪሎ ግራም በላይ የወርቅ ምርት ለብሔራዊ ባንክ ቀረበ
ጋምቤላ፤ ሰኔ 11/2013 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል ባለፉት 11 ወራት ከአንድ ሺህ 119 ኪሎ ግራም በላይ የወርቅ ምርት ለብሔራዊ ባንክ መቅረቡን የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።
ገቢ ከተደረገው የወርቅ ምርት ከ87 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጪ ምንዛሬ እንደሚያስገኝም ኤጀንሲው ገልጿል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አኳታ ቻም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ገቢ የተደረገው የወርቅ ምርት የተገኘው በክልሉ ዲማ፣ ጋምቤላ፣ መንጌሽ እና የአቦቦ ወረዳዎች በባህላዊ ወርቅ አምራቾች የተመረተ ነው።
በበጀት ዓመቱ የተገኘው የወርቅ ምርት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ854 ኪሎ ግራም በላይ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ የተሻለ የወርቅ ምርት ሊሰበሰብ የቻለው ኤጀንሲው ከወረዳዎች ጋር በመቀናጀት የተጠናከረ የክትትልና ድጋፍ ስራዎች በመከናወናቸውና አምራቾችን ለመሳብ የወርቅ ዋጋ በመሻሻሉ ነው ብለዋል።
እንዲሁም የኮንተሮባንድ አዘዋዋሪዎች ላይ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር መጠናከሩም አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።
በቅርቡ የነዳጅና ማዕድን ሚኒስትር ኢነርጂ ታከለ ኡማ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጋር በመሆን በወርቅ ማምረቻ ቦታዎች በመገኘት ያደረጉት ጉብኝት ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት እንደሚያሳይም ጠቅሰዋል።
በሚኒስቴሩና ክልሉ መንግስት የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ ዘርፉን የማዘመን ስራዎች ከተከናወነ በቀጣይ የተሻለ ወርቅ ምርት ሊገኝ እንደሚችል ዳይሬክተሯ አስረድተዋል።
በዲማ ወረዳ በባህላዊ የወርቅ ማምራት ተሰማርተው ከሚገኙ ሰዎች መካከል ወጣት ኪዳኔ ቱሳ በሰጠው አስተያየት፤ አሁን ላይ የወርቅ ዋጋ በመጨመሩ የተሻለ ለማምራት መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል ።
እንደ ወጣቱ ገለፃ፤ በቀን እስከ አምስት ግራም ወርቅ ይገኛል፤ ከዘርፉ በሚያገኘው ገቢ የራሱንና ቤተሰቡን ህይወት እየለወጠ ነው።
በአንድ ወር ውስጥ እስከ 25 ግርም ወርቅ እንደሚገኝና ከወርቅ ሽያጭ እየቆጠበ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ሌላው ባህላዊ ወርቅ አምራች ወጣት ያቆብ ወንድሙ ነው።