ቀጥታ፡

ሳዑዲ ዓረቢያ በኮቪድ-19 ወረርሽን ሳቢያ የሃጅ ጉዞን ሰረዘች... የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2013/2013(ኢዜአ) ሳዑዲ ዓረቢያ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ከኢትዮጵያ የሚደረግ የሀጅ ጉዞን መሰረዟን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

የምክርቤቱ ስራአስፈጻሚና የሀጅና ኡምራ ጉዞ አስተባባሪ ዶክተር ጄላን ገመዳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዓለም ላይ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ዘንድሮ ወደ ሀጅ የሚደረግ ጉዞ መሰረዙን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሀጅ ተጓዦችን ለማስተናገድ ዝግጅት ሲያደርግ ቢቆይም የሳዑዲ ዓረቢያ ኤምባሲ ይፋ ባደረገው መመሪያ አገሪቷ ተጓዦችን እንደማትቀበል አሳውቋል ብለዋል፡፡

ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ይህን በመረዳት ለፓስፖርትና ለተለያዩ የሀጅ ጉዳዮች የሚያደርገውን ዝግጅት በማቆም ከእንግልትና ከአላስፈላጊ ወጪ እንዲታቀብም መክረዋል።

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት የዘንድሮው የሀጅ ሥነ-ስርዓት በአገሪቷ ዜጎችና በሳዑዲ ዓረቢያ በሚኖሩ ውስን የውጭ አገራት ዜጎች ብቻ እንደሚከናወን መግለጹንም ነው ዶክተር ጄላን ያስረዱት፡፡

የዓለም ስጋት የሆነው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዲጠፋ ሁሉም የእምነት ተቋማት ጸሎት ማድረግና የራሳቸውን ጥንቃቄ መውሰድ እንዳለባቸውም መክረዋል።

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ በፊት በየዓመቱ ስምንት ሺህ ያህል ዜጎች ለሀጅና ኡምራ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ይጓዙ እንደነበር ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም