መገናኛ ብዙኃን የምርጫ ሕግና የሙያ ስነ-ምግባርን ባከበረ መልኩ ፓርቲዎችን አስተናግደዋል - የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙኃን የምርጫ ሕግና የሙያ ስነ-ምግባርን ባከበረ መልኩ ፓርቲዎችን አስተናግደዋል - የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን
አዲስ አበባ ሰኔ11/2013(ኢዜአ) መገናኛ ብዙኃን የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓላማና ፕሮግራሞቻቸውን በተሻለ መልኩ እንዲያስተዋውቁ ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ እንደገለጹት መገናኛ ብዙሃን የምርጫ ሕጉንና የሙያውን ስነ-ምግባር በተላባሰ መልኩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አስተናግደዋል።
ይህንንም የፖለቲካ ፓርቲዎችን የአየር ሠዓት አጠቃቀም አስመልክቶ የተካሄደው ጥናት ማመላከቱን ተናግረዋል።
ከመጋቢት 30 እስከ ሰኔ 9 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በ57 መገናኛ ብዙኃን የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ እጣ በማውጣት ፓርቲዎች ዓላማና ፕሮግራሞቻቸውን እንዲያስተዋውቁ ተደርጓል።
በዚሁ መሰረትም 46 የፖለቲካ ፓርቲዎችና 143 የግል እጩ ተወዳዳሪዎች በተሰጣቸው ድልድል በመገናኛ ብዙሃኑ ተስተናግደዋል።
እንደ አቶ ግዛው ገለጻ በ14 የመገናኛ ብዙሃን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች 142 የክርክር መድረኮች ተካሂደዋል።
ባለስልጣኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴና የመገናኛ ብዙኃኑን ሚና በተመለከተ አካሄድኩት ባለው ጥናት ባለሙያዎቹ የሙያውን ስነ ምግባር በተላበሰ መንገድ ሂደቱን መምራታቸውን ገልፀዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ለፓርቲዎች ከተሰጠው የአየር ሠዓት በሬዲዮና በቴሌቪዥን በአማካይ 65 በመቶ፤ በጋዜጣ 34 ነጥብ 3 በመቶ መጠቀማቸውን አብራርተዋል።
በባለስልጣኑ የግል ሚዲያ ሞኒተሪንግ ዳይሬክተር አቶ ደሬሳ ተረፈ በበኩላቸው የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀሙ በፓርቲዎች ደረጃ ሲታይ አገራዊ ፓርቲዎች የተሻለ አጠቃቀም እንደነበራቸው ጠቁመዋል።
በአንዳንድ ክልሎች የመገናኛ ብዙሃን ባለመኖራቸው አጠቃቀማቸው ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዘንድሮ ከቀደመው ጊዜ በተለየ የመገናኛ ብዙሃን ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ ከፍተኛ የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ ጥቅም ላይ መዋሉንም ተናግረዋል።
ፓርቲዎች ዓላማና ፕሮግራሞቻቸውን በ10 የአገር ውስጥ ቋንቋዎች እንዲያቀርቡ በማድረግ ህብረተሰቡ እንዲያውቀው ጥረት መደረጉንም ጠቅሰዋል።
በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት አምስት ቅሬታዎች ቀርበው ሁሉም ምላሽ ማግኘታቸውንም አብራርተዋል።
የምረጡኝ ቅስቀሳ ይዘትን በተመለከተ በተነጻጻሪ ካለፉት ጊዚያት የተሻለ ህግ አክባሪነት የተስተዋለበት መሆኑንም ነው የገለጹት።
በአጠቃላይ ለዘንድሮው አገራዊ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የመገናኛ ብዙሃን የተናበበ የአየር ሠዓት አጠቃቀም እንደተስተዋለ ባለስለጣኑ አስታውቋል።