ከመተከል ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው መመለስ ጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
ከመተከል ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው መመለስ ጀመሩ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11 ቀን 2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ከዳንጉርና ማንዱራ ወረዳዎች ተፈናቅለው በቻግኒ መጠለያ ጣቢያ የነበሩ ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ስራ ተጀመረ።
ተፈናቃዮቹ ወደ ቀዬአቸው ሲመለሱ የሚጠቀሙባቸው መሰረታዊ ፍላጎቶችና መሰረተ ልማቶች ቀደም ሲል መዘጋጀቱ ተጠቁሟል።
የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥና የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት አባል ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ "የእነዚህን ወገኖች ደህንነት ለመጠበቅ ሠራዊቱ ሙሉ ዝግጅቱን አጠናቋል" ብለዋል።
በመጠለያ ጣቢያ የቆዩት ወገኖች ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው ሕይወታቸውን መምራት እንዲችሉ ባለፉት ወራት የተለያዩ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየቱን ገልጸው፤ የአካባቢው ማኅበረሰብም ወገኖቹን ለመቀበል የተለያዩ ዝግጅቶችን ስለማድረጉ አመላክተዋል።
ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖች ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው ሕይወታቸውን እንዲቀይሩ የማይፈልጉ አካላት መኖራቸውን የጠቆሙት ብርጋዴር ጄኔራሉ፤ በወገኖቻቸው ስቃይ የሚነግዱ አካላትን ታሪክ እንደሚፋረዳቸው ተናግረዋል።
ወደ ቀዬአቸው በመመለስ ላይ ለሚገኙት ወገኖች መሰረታዊ አቅርቦቶችን ከማሟላት ባለፈ የአገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት ለደህንነታቸው ሙሉ ጥበቃ እንደሚያደርጉላቸውም አረጋግጠዋል።