ቀጥታ፡

ባህር ዳር ከነማ እግር ኳስ ክለብ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ዘመናዊ አውቶቡስ ተበረከተለት

ባህር ዳር፤ ሰኔ 10/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ፕሪሜር ሊግ ተሳታፊ ለሆነው የባህር ዳር ከነማ እግር ክለብ ለመጓጓዣ አገልግሎት የሚውል ዘመናዊ አውቶቡስ ከአማራ ክልል መንግስት በድጋፍ ተበረከተለት።

የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ባዘዘው ጫኔ የክልሉን መንግስት በመወከል ባደረጉት ንግግር  የባህርዳር እግር ኳስ ክለብ ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

ክለቡ ወደ ፕሪሜርሊግ ሲያድግ በተገባው ቃል መሰረት ዘመናዊ የመጓጓዣ አውቶቡስ  የተበረከተለት መሆኑን ተናግረዋል።

ድጋፍ የተደረገው ዘመናዊ አውቶብስ "ጎልደን ድራጎን 2019" ሞዴል ሲሆን ፍሪጅ፣ የደህንነት ካሜራና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ቁሳቁሶች የተሟሉለት መሆኑን አስረድተዋል።

"ክለቡ የክልሉና የሀገር ሃብት በመሆኑ አቅሙን በዛው ልክ ለማሳደግ የክልሉ መንግስ በቀጣይነት ይሰራል "ያሉት አቶ ባዘዘው የክለቡ ቦርድና የደጋፊ ማህበሩም በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ  ዶክተር ድረስ ሳህሉ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ያደረገው ድጋፍ ክለቡ ያለበትን የመጓጓዣ ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል  መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት የገባው ቃል በተለያዩ ምክንያቶች ቢዘገይም 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የተገዛን አውቶቡስ በማስረከቡ በክሉቡና በደጋፊ ማህበሩ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

"የክልሉ መንግስት ያበረከተው የመጓጓዣ አውቶቡስ የክለቡ አባላትን ለውጤት የሚያበቃና ተነሳሽነትን ለመፍጠር የሚያስችል ነው" ያሉት ደግሞ የእግር ኳስ ክለቡ ስራ አስኪያጅ  አቶ ልዑል ፈቃዱ ናቸው።

አውቶቡሱ ዘመናዊ በመሆኑ በረጅም ጉዞ ላይ የክለቡ አባላት ላይ የሚደርስ ድካምን ለመቀነስ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

የባህር ዳር ከነማ ስፖርት ክለብ በ1973 ዓም እንደተመሰረተ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም