"ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ መምጣት አለበት" - ኢትዮጵያ - ኢዜአ አማርኛ
"ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ መምጣት አለበት" - ኢትዮጵያ
ሰኔ 10/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አስመልክቶ የሶስትዮሽ ድርድር ሲያካሄዱ ቢቆዩም በተደጋጋሚ እየተቋረጠ ተጨባጭ ስምምነት ላይ መድረስ ያለመቻላቸው በተለያየ መንገድ የተገለጸ ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ በአፍሪካ ውስጥ የሚገደብና የአፍሪካውያን መለያ በመሆኑ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት ጉዳዩ እንዲታይ አቋሟን በአጽንኦት ገልጻለች።
"ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ መምጣት አለበት" በሚል ኢትዮጵያ ጥሪ ስታቀርብም ቆይታለች።
በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት የሚካሄደው ድርድር ሶስቱን አገራት አሸናፊ ማድረግ የሚያስችል መፍትሔ ያመጣል የሚል እምነትም እንዳላት አሳውቃለች።
በመጨረሻም ሦስቱ አገሮች በአፍሪካ ሕብረት አማካኝነት ድርድሩ ለማካሄድ በመስማማታቸው ከሰኔ 2012 ዓ.ም ሕብረቱ የማደራደር ኃላፊነቱን ወስዷል።
ድርድሩ እ.አ.አ በ2020 የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር በነበሩት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ስሪል ራማፎሳ እንዲሁም እ.አ.አ በ2021 የሕብረቱን ሊቀ መንበርነት በተረከቡት የዴሞክራቲክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፈሊክስ ቲሺኬዲ አማካኝነት ሲከናወን መቆየቱ ይታወሳል።
የሕብረቱ ድርድር በተለያዩ ምክንያቶች እየተቋረጠ ቆይቷል፡፡
ዳግም በመጋቢት 2013 ዓ.ም በዴሞክራቲክ ኮንጎ መዲና ኪንሻሳ የተካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር ያለ ስምምነት ከተጠናቀቀ በኋላ እስከአሁን መቀጠል አልቻለም።
ኢትዮጵያ የኪንሻሳው ድርድር ላይ ግብጽና ሱዳን "ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች በድርድሩ ላይ ይሳተፉ እንዲሁም አስገዳጅ ስምምነት ይፈረም" በሚል በያዙት አቋም ውጤት ሳያመጣ መቆየቱን ገልጻለች። ይህን ሀሳብ አሁንም እያስተጋቡት ይገኛል።
የሶስትዮሽ ድርድሩ አጀንዳ የግድቡ ውሃ ሙሌትና ስራ (ኦፕሬሽን) ሆኖ ሳለ ግብጽና ሱዳን ጉዳዮን ከአባይ ወንዝ ጋር ማያያዛቸው ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም በኢትዮጵያ በኩል ይጠቀሳል።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሚያዚያ 7 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ፤ በኪንሻሳው ድርድር ግብጽና ሱዳን "ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች ከአፍሪካ ሕብረት እኩል የአደራዳሪነት ሚና ይኑራቸው" በሚል ያቀረቡት ሀሳብ ለሕብረቱ ክብር አለመስጠት መሆኑን ገልጸው ነበር።
ሁለቱ አገራት ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ ውስጥ እንዳይሳካ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ "ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት መፍትሔ ያገኛል" ብላ ስለምታምን በሕብረቱ ማዕቀፍ ድርድሩ እንዲቀጥል ጥረት እንደምታደርግ ነው የገለጹት።
በተጨማሪም ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ትናንት በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ፤ ታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የአረብ ሊግ ያሳለፈው ኢ- ፍትሐዊ ውሳኔ ግብጾች ለበርካታ ዓመታት ሲደክሙበት የነበረና ከመርህ ውጭ የሆነ ጉዳይ ነው።
እርሳቸው እንዳሉት፤ ዓረብ ሊግ የሌሎች የናይል ተፋሰስ አገራትን ወደ ጎን በመተው የግብጽና የሱዳንን ጥቅም ብቻ ለማስከበር ያሳለፈው ውሳኔ ኢ-ፍትሐዊ ነው።
የደቡብ ሱዳን የውሃ ሀብትና መስኖ ሚኒስትር ሚስተር ማናዋ ፒተር ጋትኩት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሶስትዮሽ ድርድር ያሏቸውን አለመግባባቶች በውይይት ብቻ መፍታት እንደሚጠበቅባቸው ነው የገለጹት።
ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ትክክለኛው አካሄድ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡
ግብጽ ወደ ናይል ቤዚን የትብብር ማዕቀፍ መምጣት እንዳለባትና በውሃ ሀብት አጠቃቀም ላይ ያሉ ጉዳዮች በማዕቀፉ ስር መፍትሔ ማግኘት እንደሚችሉ ገልጸዋል።
ደቡብ ሱዳን የፈረመችውን የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት በአገሪቷ ፓርላማ ለማጽደቅ በሰላም ስምምነቱ መሰረት የላይኛውና የታችኛውን የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ካደራጀች በኋላ የሚታይ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የሶስትዮሹ ድርድር በህብረቱ አማካኝነት በማድረግ ጉዳዩ መቋጫ እንዲበጅለት ሙሉ ፍላጎት እንዳላት ደጋግማ አሳውቃለች። ከዚህ ጥረት በተጓዳኝ ደግሞ ግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌቱን እንደሚያካሂድ አስታውቃለች።
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በኩላቸው፤ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ የሚከናወን መሆኑን አረጋግጠዋል።
"የውሃ ሙሌቱ ተፈጥሯዊ ሂደቱን ጠብቆ መሞላቱ ላይ ምንም አይነት ክርክር የሚያስነሳ ጉዳይ የለም። የሶስቱ አገራት የውሃ ባለሙያዎችም ይሄን ጉዳይ በግልጽ ያውቁታል" ብለዋል ሚኒስትሩ።
የሱዳን መስኖና የውሃ ሀብት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ያሲር አባስ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ሱዳን ኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ኤሌክትሪክ የማመንጨት መብቷን ታከብራለች። በዚህ ላይ ያላት አቋም ተመሳሳይ ነው።
ሱዳን እ.አ.አ በ2015 በተፈረመው የመርሆች ስምምነት አማካኝነት በግድቡ ሙሌትና ስራ (ኦፕሬሽን) ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ላይ መድረስ እንደምትፈልግ ተናግረዋል።
ሱዳን ከሕዳሴ ግድቡ የውሃ ሙሌት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ከኢትዮጵያ እንደምትፈልግና ይሄም ለሮሴሪስ ግድቧ ደህንነት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ከመጀመሯ በፊት መረጃ ለመለዋወጥ እንዲቻል ሱዳንና ግብጽ ባለሙያዎችን እንዲሰይሙ ያቀረበችውን ጥያቄ ሁለቱ አገራት አለመቀበላቸው ይታወሳል።
በናይል ተፋሰስ አገራት ያሉ የውሃ ሀብቶች አጠቃቀም ላይ ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖር የማድረግ አላማ ያለው የናይል ቤዚን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እ.አ.አ በ2010 መዘጋጀቱ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ፣ሩዋንዳ፣ታንዛንያ፣ዩጋንዳ፣ደቡብ ሱዳን፣ኬንያና ብሩንዲ ስምምነቱን ፈርመዋል።
ስምምነቱን ከፈረሙት አገራት መካከል ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያና ዩጋንዳ ስምምነቱን በአገራቸው ፓርላማ አጽድቀውታል።
የናይል ቤዚን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ሕግ ሆኖ ወደ ስራ እንዲገባ ስድስት አገራት በአገራቸው ፓርላማ ማጽደቅ ይጠበቅባቸዋል።